የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር አዲስ ስራ አስፈጻሚዎች ተሾሙላቸው

በሃሚድ አወል

በኢትዮጵያ በባቡር መሰረት ልማት እና የትራንስፖርት ዘርፍ ለተሰማሩ ሁለት የመንግስት መስሪያ ቤቶች አዲስ የስራ አስፈጻሚዎች ተሾሙላቸው። ህሊና በላቸው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን እንዲመሩ ሲሾሙ፤ ዶ/ር አብዲ ዘነበ ደግሞ የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነዋል። 

ህሊና በላቸው የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን በዋና ስራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት መጋቢት 13፤ 2014 መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አበበች ድሪባ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አዲሷ ተሿሚ የባቡር ኮርፖሬሽን ኃላፊነት ከመረከባቸው በፊት በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈጻሚነት ሰርተዋል። በኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝም ለሶስት ዓመታት ያህል በምክትል ስራ አስኪያጅነት አገልግለዋል። 

የባቡር ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን የመገንባት እና የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት ዓላማ አንግቦ የተቋቋመውን ኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን ላለፉት ሶስት ዓመታት በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ናቸው። ዶ/ር ስንታየሁ ለሶስት ዓመታት ያህል የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የመንግስት ፋይናንስ ተቋማት ኤጀንሲንም በዳይሬክተርነት መርተዋል።

ከ14 ዓመታት በፊት በ2000 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣ ደንብ የተቋቋመው የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የመጀመሪያ ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት ዶ/ር ጌታቸው በትሩ ናቸው። ኮርፖሬሽኑ መቶ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የባቡር መስመር ፕሮጀክቶች ግንባታዎችን በበላይነት በመራበት ወቅት ዶ/ር ጌታቸው ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።    

ለሰባት ዓመታት ያህል ኮርፖሬሽኑን የመሩት ዶ/ር ጌታቸው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ስራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ የመንግስታዊውን ድርጅት ኃላፊነት ቦታ የተረከቡት ዶ/ር ብርሃኑ በሻህ ነበሩ። ተተኪው ዋና ስራ አስፈጻሚ በኃላፊነት ቦታው ላይ መቆየት የቻሉት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ብቻ ነው።

ዶ/ር ብርሃኑ ራሳቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ከኃላፊነታቸው ከለቀቁ በኋላ በኮርፖሬሽኑ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት አቶ የኋላሸት ጀመረ ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ለአንድ ወር ሰርተዋል። የኢኮኖሚክስ ምሩቁ ዶ/ር ስንታየሁ ወልደሚካኤል የኮርፖሬሽኑ ሶስተኛው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ለሶስት ዓመት አገልግለዋል። ዶ/ር ስንታየሁ  ከኮርፖሬሽኑ ስራ አስፈጻሚነት ከተነሱ በኋላ በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተሹመዋል። 

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሹመት ይፋ ከተደረገ ከ10 ቀናት በኋላ በባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የተሰማራው የሌላኛው የመንግስት መስሪያ ቤትም የአመራር ለውጥ አድርጓል። በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መንግስታት ስምምነት መሰረት ከአምስት ዓመት በፊት የተመሰረተው የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር አዲስ ዋና ስራ አስፈጻሚ የተሾመለት መጋቢት 23፤ 2014 ነው።

የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ፊርማ መሾማቸው የተገለጸው አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብዲ ዘነበ ናቸው። ዶ/ር አብዲ በዋና ስራ አስፈጻሚነት ከመሾማቸው በፊት በሰላም ሚኒስቴር እና በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሰርተዋል። ከአዲስ አበባ በፖለቲካ ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ዶ/ር አብዲ፤ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በመምህርነት አገልግለዋል። 

ዶ/ር አብዲ አዲሱን የኃላፊነት ቦታ የተረከቡት፤ የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበርን ከምስረታው ጀምሮ በዋና ስራ አስፈጻሚ ያገለገሉትን አቶ ጥላሁን ሳርካን በመተካት ነው። ተሰናባቹ አቶ ጥላሁን በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በምክትል ስራ አስፈጻሚነት፤ እንዲሁም በደቡብ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በስራ አስኪያጅነት የሰሩ ነበሩ። አቶ ጥላሁን አራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተደረገበትን የኢትዮ ጅቡቲን የባቡር መስመር የማስተዳደር ኃላፊነት ሲወጡ ቆይተዋል።

አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር የተገነባው፤ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በተፈራረሙት የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት ነው። በሁለት የቻይና ኩባንያዎች ግንባታው የተከናወነውን የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር ሰባ ከመቶ ወጪ የተሸፈነው ከቻይናው ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)