የሀገራዊ የምክከር ኮሚሽን፤ ፍኖተ ካርታ እና ዝርዝር ዕቅድ እንዲያዘጋጅ በፓርላማ ተጠየቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ፍኖተ ካርታ እና ዝርዝር ዕቅድ እንዲያዘጋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠየቀ። ኮሚሽኑ ጥያቄው የቀረበለት ዛሬ ማክሰኞ ሚያዚያ 18፤ 2014 ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤዎች እና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ሪፖርት ካቀረበ በኋላ ነው። 

በኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የቀረበው ሪፖርት፤ ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት ዘርዝሯል። ኮሚሽኑ ስራዎቹን በማከናወን ላይ የሚገኘው በአራት ምዕራፎች ከፋፍሎ መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢው፤ አሁን ከሚገኝበት የዝግጅት ምዕራፍ አስቀድሞ የነበሩ ሂደቶችን አብራርተዋል።  

በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ኮሚሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ መሾሙን እና ሰራተኞችን በጊዜያዊነት መመደቡን ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል። የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሰራተኞችን ያገኘው ንብረታቸውን ጭምር ከተረከበው የእርቀ ሰላም እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽኖች መሆኑንም ሰብሳቢው ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በዝግጅት ምዕራፉ፤ አስራ አንዱንም ኮሚሽነሮች በአባልነት ያቀፈው የኮሚሽኑ ምክር ቤት በሚያወጣው መስፈርት መሰረት የአወያዮች እና የአመቻቾች ምልመላ እንደሚያከናውን ፕሮፌሰር መስፍን ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል። ኮሚሽኑ በምልመላ ለተለዩት አወያዮች እና አመቻቾች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥም አክለዋል።

በዝግጅት ምዕራፍ ከሚከናወኑ የኮሚሽኑ አበይት ተግባራት ውስጥ የአጀንዳ ቀረጻ ዝግጅት፣ ልየታ እና ቅድመ ተከተል ማስያዝ ተግባራት እንደሚገኙበትም በዛሬው ስብሰባ ላይ ተገልጿል። ለኮሚሽኑ የሚመደበውን በጀት ዝግጅትም እንዲሁ በዚሁ ምዕራፍ ወቅት ይጠቃለላል ተብሏል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁትን የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እና የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ቢሮዎች እና ንብረቶች ሲረከብ፤ ለሁለቱ ኮሚሽኖች ለ2014 የተመደበላቸውን በጀትም እንዲዛወርለት ተደርጓል። የአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለ2014 የተመደበለት በጀት 25.7 ሚሊዮን ብር ሲሆን የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ደግሞ 21.4 ሚሊዮን ብር ተበጅቶለት ነበር። 

የምክክር ኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፉን ሲያጠናቅቅ ወደ ምክክር ሂደት የሚገባ መሆኑን ሰብሳቢው ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል። የሶስት ዓመት የስራ ዘመን እንዲኖረው ተደርጎ በአዋጅ የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽኑ በእቅዱ በመጨረሻነት የያዘው፤ የምክክር ውጤቶችን የመተግበሪያ ምዕራፍን ነው።  

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ የዛሬውን ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና አፈ ጉባኤዎች፤ ያላቸውን አስተያየት እና ጥያቄ ሰንዝረዋል። አንድ ሰዓት ገደማ ያህል በወሰደው የጥያቄ ማቅረቢያ ክፍለ ጊዜ የተነሱት አብዛኞቹ አስተያየቶች በኮሚሽኑ ፍኖተ ካርታ እና ዕቅድ ዝግጅት ላይ ያተኮሩ ነበሩ። 

የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ በአራት ምዕራፍ የተከፋፈለው የኮሚሽኑ ስራ የሚመራበትን ፍኖተ ካርታ ማየት ይቻል እንደሆነ ጥያቄ አቅርበዋል። ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ እና በፓርላማ የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጅጌም በተመሳሳይ ኮሚሽኑ ፍኖተ ካርታውን ማዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል። 

አቶ ተስፋዬ፤ ኮሚሽኑ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀቱ ላይ ሁለት ነገሮችን ታሳቢ ማድረግ እንዳለበት በተጨማሪነት አንስተዋል። ፍኖተ ካርታው ተጣድፎ የሚሰራ ከሆነ “የስራውን ግዙፍነት የማይመጥን እንዳይሆን” ስጋት እንዳላቸው የገለጹት የመንግስት ተጠሪው፤ ሂደቱ “የስራውን Quality [ጥራት] የሚነካ” መሆን እንደማይገባው አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህም ሆኖ ግን ፍኖተ ካርታውን ማዘጋጀቱ ብዙ ጊዜ ሊወስድ እንደማይገባው አስገንዝበዋል።  

በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለም፤ ኮሚሽኑ “ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ፤ ምን፣ መቼ እና እንዴት ሊተገብር እንዳሰበ ዕቅዱን ማቅረብ ይኖርበታል” ሲሉ የሌሎቹን አስተያየት ሰጪዎች ሃሳብ ተጋርተዋል። “አጠቃላይ የዝግጅት ሂደቱ ከውጤቱ እኩል አስፈላጊ ስለሆነ ፍኖተ ካርታው ላይ አጽንኦት ቢሰጥ” ሲሉም ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።  

የህግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ እጸገነት መንግስቱም በተመሳሳይ፤ ኮሚሽኑ “ልቅም ያለ ሊያሰራ የሚችል” የሶስት ዓመት ዕቅድ ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል። የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ኮሚሽኑ የሚያዘጋጀው ዕቅድ “በየትኛው ወራት ምን እንደሚሰራ ሊያሳይ የሚችል መሆን አለበት” ሲሉም አክለዋል።  

ከፓርላማ አባላቱ በተነሱ ሃሳቦች ላይ አስተያየት እና ምላሽ የሰጡት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ የምክክር ኮሚሽኑ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፤ ፍኖተ ካርታውን በዛሬው ስብሰባ ያላቀረቡት “ያልተጣራ road map” ይዘው መምጣት ባለመፈለጋቸው መሆኑን ተናግረዋል። በፍኖተ ካርታው ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ “በቅርቡ” ለፓርላማ እንደሚቀርብም ቃል ገብተዋል። 

“ሁሉን አቀፍ እና አካታች” ምክክር ያካሄዳል የተባለውን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያቋቋመው አዋጅ የጸደቀው ከአራት ወር በፊት ታህሳስ 20፤ 2014 ነበር። ከአዋጁ መጽደቅ ሁለት ወራት ገደማ በኋላ ኮሚሽኑን በበላይነት የሚመሩት 11 ኮሚሽነሮች የካቲት 14፤ 2014 በፓርላማ መሾማቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)