በተስፋለም ወልደየስ
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) “በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ 297 ሰዎች በመንግስት ታጣቂዎች ተገድለዋል” ሲል ወነጀለ። ፓርቲው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው ባለው “ደም አፋሳሽ ጦርነት” ምክንያት ከ500 ሺህ ሰዎች በላይ መፈናቀላቸውን አስታውቋል።
ኦፌኮ ይህን ያለው ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 4፤ 2014 ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ነው። ፓርቲው በመግለጫው ቅድሚያ የሰጠው በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ይስተዋላላሉ ላለቸው “የፖለቲካ ውድቀት፣ የእርስ በእርስ ጦርነት እና የኢኮኖሚ ቀውስ” ክስተቶች ነው።
እነዚህ እርስ በእርስ የተሳሰሩ ክስተቶች “ኢትዮጵያን እያናጉ ያሉ አዙሪቶች ናቸው” ያለው ኦፌኮ፤ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔው በሀገሪቱ ያለውን የእርስ በእርስ “ጦርነት በማስቆም ችግሮችን ወደ ፖለቲካ ድርድር መድረክ ማምጣት ነው” ሲል ከችግሮቹ መውጫ መንገዱን ጠቁሟል። ፓርቲው በኢትዮጵያ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት መቋጫ ካላገኘ፤ “የሀገሪቱ ፖለቲካው እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የበለጠ እየጠነከረና እየተወሳሰበ መሄዱ አይቀርም” ሲልም አስጠንቅቋል።
ኦፌኮ በዚሁ መግለጫው ፓርቲው በዋነኝነት በሚንቀሳቀስበት የኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄዱ ናቸው ባላቸው ጦርነቶች ምክንያት የደረሱ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶችን ዘርዝሯል። ፓርቲው “ላለፉት አራት ዓመታት ሰላምና መረጋጋት አግኝቶ አያውቅም” ሲል በጠቀሰው በኦሮሚያ ክልል፤ ባለፉት ወራት ጥቂት ወራት ብቻ “ከ297 በላይ ንጹሃን ዜጎች” ተገድለዋል ብሏል።
ተቃዋሚው ፓርቲ ለእነዚህ ግድያዎች ተጠያቂ ያደረገው “የመንግስት ታጣቂዎች” ያላቸውን ነው። የመንግስት ታጣቂዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከኦሮሚያ ውጭ “በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች” እንደሚስተዋል የጠቆመው ኦፌኮ ድርጊቱን በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል። ፓርቲው በእነዚህ አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ተፈጽመዋል ያላቸው “የጅምላ ግድያዎች” ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲጣሩ እና ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።
በኦሮሚያ ክልል ባሉ ዜጎች ላይ ከሚፈጸሙ ግድያዎች እና መፈናቀሎች በተጨማሪ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙ ኦፌኮ በመግለጫው ዘርዝሯል። “[በኦሮሚያ] ሰዎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በገፍ ይታሰራሉ፤ ማሰቃየት ይፈጽምባቸዋል፤ ከፊሎቹ ያለፍርድ ይገደላሉ፤ የተወሰኑት ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደርገዋል” ሲል ኦፌኮ በመግለጫው ወንጅሏል። በኦሮሚያ ክልል “የፍትህ ስርዓቱ እጅጉን ተዳክሟል” ሲል የሚከስሰው ኦፌኮ፤ ለዚህም በፍርድ ቤት የሚተላለፉ ውሳኔዎች “ብዙውን ጊዜ በአስተዳደር አካላት ችላ እንደሚባሉ” በማሳያነት አንስቷል።
ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በላይ የወሰደው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት “በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ ለሚሊዮኖች መፈናቀል እና በመቶ ቢሊዮን ብሮች ለሚገመት ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል” ያለው ኦፌኮ፤ ጦርነቱ “ሀገሪቱንም ወደ ፍጹም ውድቀት እንድታመራ አድርጓታል” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል። “ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ አሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በዋነኛነት በጦርነት የተጠቁ ሲሆኑ ሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች በጦርነቱ መዘዝ እየተሰተቃዩ ነው” በማለትም ፓርቲው የጦርነቱ ዳፋ በርካታ አካባቢዎችን ማካለሉን ጠቁሟል።
“በጦርነቱ ምክንያት ሀገሪቱ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውድቃለች። አርሶ አደሮችን የሚቀጥለውን ምርት ማምረት አልቻሉም፣ የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የዋጋ ንረት፤ ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ መጠን መቀነስ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የካፒታል ከሀገር መሸሽ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መቀነስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲል ኦፌኮ ጦርነቱ ያስከተላቸውን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዘርዝሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)