የአማራ ክልል መንግስት የጸጥታ ምክር ቤት በክልሉ እየተስፋፋ መጥቷል ያለውን “ህገወጥነትን ለመቆጣጠር እና ህግን ለማስከበር” በየደረጃው የጸጥታ ኃይሎች እንዲቋቋሙና እርምጃ እንዲወስዱ ውሳኔ አሳለፈ። የጸጥታ ምክር ቤቱ ትላንት አርብ ግንቦት 5 ባደረገው ስብስባ “ሕገ-ወጦችን እና ሥርዓት አልበኞች” ያላቸውን አካላት መቆጣጠር እና የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ “ግንባር ቀደም የትኩረት አቅጣጫ እንዲሆን” ከውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውቋል።
የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት በትላንትና ስብሰባው የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ በጥልቀት መገምገሙ ተገልጿል። ምክር ቤቱ ከስብሰባው መገባደድ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ “የወያኔ ወረራ ቡድን” ሲል የጠራው ኃይል “በአማራ ክልል ላይ ዳግም ጦርነት አውጇል” ሲል ከስሷል። ይህን ጦርነት “ለመመከት እና ለመቀልበስ” እንዲቻልም፤ በክልሉ “በየደረጃው ያለው የጸጥታ መዋቅር ዝግጁ መሆን እንዳለበት” ምክር ቤቱ “አቅጣጫ ማስቀመጡን” አመልክቷል።
ምክር ቤቱ በአማራ ክልል ላይ ሊሰነዘር ይችላል ስላለው ጥቃት በመግለጫው ላይ ቢያነሳም ሰፊውን ቦታ ሰጥቶ የዳሰሰው ግን በክልሉ “ስር እየሰደደ መጥቷል” ስላለው “ህገ ወጥነት እና ሥርዓት አልበኝነት” ነው። በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች “ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር” እየተስፋፋ መምጣቱን የጠቀሰው ምክር ቤቱ፤ ይህ ሁኔታ “የክልሉን ሰላም ደህንነት ስጋት ውስጥ እየጣለ ይገኛል” ብሏል።
በአማራ ክልል ሕገ ወጥ ታጣቂዎች እያደረጉት ነው በተባለው “ያልተገባ እንቅስቃሴ” ምክንያት፤ የክልሉ ልማቶች እየተዳከሙ፣ የዜጎች በነጻነት የመንቀሳቀስ ሁኔታ እየተገደበ፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እየተዘጉ እና የተፈጠሩ የስራ ዕድሎች እየጠፉ መምጣታቸውን ምክር ቤቱ ዘርዝሯል። ይህ አካሄድ “የአማራ ክልልን ልማት በአደገኛ ሁኔታ እየተፈታተነ ይገኛል” ያለው የጸጥታ ምክር ቤት፤ በክልሉ ለሚካሄዱ ቀጣይ ልማቶችም እንቅፋት መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።
“እነዚህን ህገ-ወጥ ተግባራት በከተማም ሆነ በገጠር በአጭር ጊዜ ማረም ካልተቻለ የአማራ ክልል ልማት የሚያስቀጥል ሳይኾን የነበረውንም የሚያመክን፤ የህገ-ወጥነትና የሥርዓት አልበኝነት መናኸሪያ የሚያደርግ መኾኑን በመረዳት፤ ለሕዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል መልክ መያዝ እንዳለባቸው ታምኖበታል” ሲል የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት መግለጫ አትቷል።
የአማራ ክልል መንግስት ከህዝብ ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች፤ የህግ የማስከበር ስራውን በጥብቅ እንዲፈጽም እና ሰላምና ደህንነት እንዲያስከብር ተደጋጋሚ ጥያቄዎች መቅረባቸውን መግለጫው አስታውሷል። የክልሉ መንግስት እነዚህን ጥያቄዎች ከመረመረ በኋላ “ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን” እንዳመነበት መግለጫው ጠቁሟል።
ይህን ተንተርሶም በክልሉ ያሉ “ሕገ-ወጦችን እና ሥርዓት አልበኞችን” ለመቆጣጠር ከውሳኔ ላይ መደረሱን የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት ገልጿል። ሕገወጥነትን ለመቆጣጠርና ሕግን ለማስከበር እንዲቻልም የጸጥታ ኃይሎች “ተገቢ ነው” ያሏቸውን እርምጃዎች እንዲወስዱ አቅጣጫ መቀመጡንም አስታውቋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)