በአዲስ አበባ የታሰረችው ጋዜጠኛ ሰቦንቱ አህመድ ወደ ቢሾፍቱ ተወሰደች

በሃሚድ አወል

ትላንት በአዲስ አበባ ከተማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው የ“ፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ” የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ሰቦንቱ አህመድ ወደ ቢሾፍቱ መወሰዷን የጣቢያው ዋና ዳይሬክተር ተናገሩ። የጣቢያው ዋና ዳይሬክተሩ ለሚ ታዬ ጋዜጠኛዋ ዛሬ ከሰዓት ወደ ቢሾፍቱ እየተወሰደች መሆኑን በስልክ እንዳሳወቀቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

በ“ፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ” ዜና አንባቢ እና የመዝናኝ ፕሮግራም አዘጋጇ ሰቦንቱ በፖሊስ የተያዘችው፤ ትላንት ሐሙስ ግንቦት 18፤ 2014 አመሻሽ ላይ ከስራ ቦታዋ ስትወጣ መሆኑን አቶ ለሚ አስረድተዋል። በቁጥጥር ስር ያዋሏት ፖሊሶች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመያዛቸውንም አክለዋል። 

ጋዜጠኛዋ ከታሰረች በኋላ ወደ ለቡ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዷን እና እስከዛሬ ሰባት ሰዓት ድረስም በዚያው እንደነበረች ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። ሰቦንቱን በለቡ ፖሊስ ጣቢያ እያለች እንደጠየቋት የሚናገሩት አቶ ለሚ፤ የተያዘችበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዳልተገለጸላት እንደነገረቻቸው እና ፍርድ ቤትም እንዳልቀረበች አስታውቀዋል። 

የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና ዳይሬክተር የጋዜጠኛዋን እስር በተመለከተ በፖሊስ ጣቢያው የሚገኙትን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ማነጋገራቸውን ጠቅሰዋል። ፖሊሶቹ “የኦሮሚያ ፖሊስ ነው እንድትያዝ ያደረገው። እኛ በአደራ ነው ያስቀመጥናት” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸውም አቶ ለሚ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ጋዜጠኛ ሰቦንቱ ዛሬ አርብ ግንቦት 19 ከሰዓት ወደ ቢሾፍቱ መወሰዷን ከመስማታቸው ውጭ፤ በአሁኑ ወቅት በየትኛው ፖሊስ ጣቢያ እንደምትገኝ “ዝርዝር መረጃ” እንደሌላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል። የጋዜጠኛዋን እስር ተከትሎ ዛሬ ረፋድ ላይ መግለጫ ያወጣው የኦሮሚያ ጋዜጠኞች ማህበር “ባልታወቀ ምክንያት የታሰረችው ጋዜጠኛ በአስቸኳይ እንድትፈታ” ጠይቋል። 

የኦሮሚያ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ናዚፍ ጀማል፤ ሰቦንቱንም ሆነ ሌሎችንም ጋዜጠኞች “ከመንገድ ላይ መጥቶ ማሰር ተቀባይነት የለውም” ሲሉ አስተያየታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሰጥተዋል። በትላንትናው ዕለት ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ ሰቦንቱን ጨምሮ ሶስት ጋዜጠኞች በጸጥታ ኃይሎች ተይዘዋል።፡

ትላንት ሐሙስ በጸጥታ ኃይሎች የተያዙት ሌሎቹ ሁለት ጋዜጠኞች ተመስገን ደሳለኝ እና ያየሰው ሽመልስ ናቸው። የትላንቱ የሶስት ጋዜጠኞች እስር፤ በኢትዮጵያ ከሰሞኑ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ቁጥር 14 አድርሶታል። “እንደ ማህበር አንድ ጋዜጠኛ መጠየቅ የለበትም፤ መታሰር የለበትም የሚል ጭፍን አቋም የለንም” ያሉት የኦሮሚያ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት፤ ጋዜጠኛ ሲያጠፋ ሊጠየቅ የሚገባው በሀገሪቱ ህግ መሰረት መሆን አለበት ሲሉ ሂደቱ በህግ አግባብ መከናወን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

 በመጋቢት 2013 ዓ.ም. የጸደቀው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፤ “በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፤ በወንጀል ስነ ስርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ህግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት” ሲል ይደነግጋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)