የገለባት- መተማ የድንበር ኬላ ለዜጎች እንቅስቃሴ ክፍት እንዲደረግ ሱዳን ወሰነች

በገላባት እና መተማ መካከል የሚገኘው የኢትዮጵያ እና የሱዳን የድንበር ኬላ እንዲከፈት በጄነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የሱዳን የጸጥታ እና መከላከያ ምክር ቤት ወሰነ። አል-ገላባት የድንበር መተላለፊያ ከትላንት እሁድ ጀምሮ እንዲከፈት የተወሰነው የሱዳን የጸጥታ እና መከላከያ ምክር ቤት ቴክኒካዊ ኮሚቴ ካካሔደው ስብሰባ በኋላ ነው።

ውሳኔው የሁለቱ ሀገራት አመራሮች በድንበር አካባቢ ለተቀሰቀሰው ውጥረት “አፋጣኝ እና ዘላቂ” መፍትሔ ለማበጀት የጀመሩትን ውይይት መነሻ በማድረግ እንዲሁም “የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሱዳን ግዛት ሰርገው እንዳይገቡ ለመከላከል ከኢትዮጵያ በኩል ለታየው መልካም ፈቃድ ምላሽ” የተላለፈ መሆኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል። በገላባት እና መተማ መካከል የሚገኘው የድንበር መተላለፊያ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢዎች በተደጋጋሚ በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ሲዘጋ ሲከፈት የቆየ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝደንት አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ በኬንያ በተካሄደው የኢጋድ ስብሰባ ላይ በተገናኙበት ወቅት፤ በአገሮቻቸው መካከል የተቀሰቀሰውን ውጥረት ለመፍታት ንግግር መጀመራቸውን አስታውቀው ነበር። ሁለቱ መሪዎች ውይይት የጀመሩት፤ በአወዛጋቢው አል-ፋሽጋ አካባቢ ባለፈው ግንቦት ወር አዲስ ውጥረት ከተቀሰቀሰ በኋላ ነበር።

የሱዳን የጸጥታ እና መከላከያ ምክር ቤት ትላንት እሁድ ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ በሁለቱ ድንበሮች አካባቢ ያለውን ቁጥጥር ለማጥበቅ ውሳኔ መተላለፉን አስታውቋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል የትኞቹም የታጠቁ ኃይሎች እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ለመከላከል ጥብቅ ትብብር እንደሚያደርጉም መግለጫው አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)