ግብጽ በአባይ ግድብ ላይ ሲካሄድ የቆየውን የሶስትዮሽ ድርድር ሲመሩ የነበሩትን የውሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስትሯን በአዲስ ተሿሚ ተካች። የሀገሪቱን የውሃ ሃብት እና መስኖ መስሪያ ቤትን በሚኒስትርነት እንዲመሩ የተሾሙት፤ በውሃ ሃብቶች አስተዳደር ምርምሮቻቸው የሚታወቁት ዶ/ር ሄኒ ስዌይለም ናቸው።
የግብጽ ፓርላማ ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 7፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ የዶ/ር ሄኒን ጨምሮ 13 አዳዲስ ሚኒስትሮችን ሹመት አጽድቋል። የሀገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት በፕሬዝዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ የቀረበለትን የሚኒስትሮች ሹም ሽር ያጸደቀው፤ ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ ለሶስት ወራት የበጋ ዕረፍት የተበተኑት የፓርላማ አባላቱ “ለአስቸኳይ ጉዳይ” በሚል እንዲሰበሰቡ ከተጠሩ በኋላ ነው።

የካቢኔ ሹም ሽሩ የተደረገው “በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ፤ በአንዳንድ ወሳኝ ዘርፎች የመንግስትን አፈጸጸም ለማሻሻል” መሆኑን ፕሬዝዳንት አልሲሲ ተናግረዋል። በግብጽ መንግስት የተደረገው ለውጥ “የሀገሪቱን ጥቅሞች እና የማስፈጸም አቅሞችን የማስጠበቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህም “በቀጥታ ለግብጻውያን ዜጎች የሚቀርቡ አገልግሎቶችን የሚያሻሽል ይሆናል” ሲሉ አዲሱ ካቢኔ ከፍ ያለ ስራ እንደሚጠብቀው ጠቁመዋል።
ዛሬ ሹመታቸው የጸደቀው አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች የተሾሙት፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማዶብሊ ጋር ካደረጓቸው “ሰፊ ምክክሮች” በኋላ መሆኑን ፕሬዝዳንት አልሲሲ መናገራቸውን የሀገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል። በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ውሳኔ መሰረት አዳዲስ ሚኒስትሮች ከተሾሙላቸው የግብጽ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የጤና፣ ትምህርት፣ ባህል፣ ቱሪዝም፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ እንደዚሁም የወታደራዊ ምርት ሚኒስቴሮች ይገኙባቸዋል።

ግብጽ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ የአሁኑን ጨምሮ ለአምስት ጊዜ ያህል የካቢኔ ሹም ሽር አካሄዳለች። የዛሬው ካቢኔ ሹም ሽር ሰለባ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የግብጽ የውሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ሲመሩ የቆዩት መሐመድ አብደል አቲ ናቸው።
በአባይ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ባደረጓቸው ድርድሮች ሀገራቸውን በዋና ተደራዳሪነት ሲወክሉ የቆዩት መሐመድ አብደል አቲ ከስልጣናቸው የተነሱት፤ ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ማጠናቀቋን ይፋ ባደረገች በማግስቱ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ኢትዮጵያ ማስታወቋ ይታወሳል። (በተስፋለም ወልደየስ- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)