በአማራ ክልል በከተሞች ዙሪያ ባሉ ቦታዎች፤ የኢንቨስትመንት ምሪት እንዲቆም ውሳኔ ተላለፈ

በሃሚድ አወል

የአማራ ክልል በከተሞች ዙሪያ የሚሰጥ የኢንቨስትመንት ቦታ “በልዩ ሁኔታ” ካልተፈቀደ በስተቀር እንዲቆም ውሳኔ አሳለፈ። ውሳኔው የተላለፈው፤ “ያለ አግባብ የሚመራውን እና እየተመራ ያለውን የኢንቨስትመንት አካሄድ ስርዓት ለማስያዝ” እንደሆነ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ለኢንቨስትመንት የሚሰጥ ቦታ ላይ ጊዜያዊ እገዳ እንዲደረግ ውሳኔውን ያስተላለፉት፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ናቸው። ርዕሰ መስተዳድሩ ለሁሉም የክልሉ ዞኖች እና የሪጆ ፖሊታን ከተማ አስተዳደሮች ባለፈው ሰኞ ህዳር 5፤ 2015 በጻፉት ደብዳቤ፤ “በከተሞች አቅራቢያ የሚደረገው የኢንቨስትመንት አሰጣጥና ምሪት ችግሮች እየተስተዋሉበት መጥቷል” ሲሉ አስፍረዋል። 

ዶ/ር ይልቃል በዚሁ ደብዳቤያቸው፤ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ፣ ለክልል ኢንቨስትመንት ቦርድ አቅርቦ የሚያስወስነው ካልሆነ፤ በከተሞች ዙሪያ የኢንቨስትመንት ምሪት ማድረግ እንደማይቻል አስታውቀዋል። “ማንም አካል ይህን ተግባር እንዳይፈጽም እና እንዲያቆም በጥብቅ አሳስባለሁ” ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በከተሞች ዙሪያ የሚደረጉ የኢንቨስትመንት ምሪቶችን “በልዩ ሁኔታ” ተመልክቶ ውሳኔ የሚሰጠው የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ቦርድ፤ የኢንቨስትመንት ጉዳይ የሚመለከታቸውን የክልሉን ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በአባልነት ያቀፈ መሆኑን አቶ እንድሪስ ገልጸዋል። በርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራው ይህ ቦርድ፤ የክልሉን ማዕድን፣ መሬት፣ የከተማና መሰረተ ልማት እንዲሁም ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮዎችን በአባልነት የያዘ ነው። 

የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ በክልሉ መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሀብቶች “የተደራጁ ቦታዎችን” ቢለይም፤ የመሬት ምሪት የሚካሄደው ግን የኢንቨስትመንት ቦርዱ “እዚህ ቦታ ላይ ይሔንን መምራት አለብን ብሎ ይሁንታ ሲሰጥ ብቻ” መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አቶ እንድሪስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። የክልሉ ኢንቨስትመንት ምሪት “በስርዓት መመራት አለበት” የሚሉት እንድሪስ፤ “ይሄን ማስታረቅ የሚቻለው መንግስት ለኢንቨስትመንት ብሎ በለያቸው ቀጠናዎች ላይ ኢንቨስት ሲደረግ ነው” ባይ ናቸው። 

በከተሞች መሃል የኢንቨስትመንት መሬት እያለ፤ ኢንቨስተሮች በከተማ ዙሪያ ያሉ መሬቶችን እንደሚጠይቁ አቶ እንድሪስ ለዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ። “አሁን በየአርሶ አደሩ መንደር ጭምር በኢንቨስትመንት ስም ቦታዎች ታጥረው ይታያሉ” የሚሉት የቢሮ ኃላፊ፤ “ይህ ውስን የሆነውን የክልሉን የመሬት ሀብት ለፈለግነው ዓላማ ማዋልን የሚያግድ እና የከተሞችን የዕድገት ደረጃ የሚገታ ሆኖ አግኝተነዋል” ሲሉ አሁን ያለው አካሄድ መታረም የሚገባው እንደሆነ ያስረዳሉ። 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በጻፉት ደብዳቤ ላይም ይህንኑ ጉዳይ በአጽንኦት አንስተውታል። ዶ/ር ይልቃል በዚሁ ደብዳቤያቸው፤ በከተሞች ዙሪያ የሚደረገው የኢንቨስትመንት ምሪት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች፤ ክልሉ ያለውን ውስን ሀብት የሚያባክኑ፤ በፕላን የሚመሩ፣ ጽዱ፣ ለነዋሪዎች ተስማሚ፣ እውነተኛ የኢኮኖሚ ግንባታ ማሳለጫ እና የግብይት ማዕከል የሆኑ ከተሞችን የመፍጠር “የክልሉን ህልም የሚያደናቅፉ” ናቸው ብለዋል። 

በከተሞች ዙሪያ የሚደረገው የኢንቨስትመንት ምሪት የከተሞችን እድገት “በሚገታ እና በሚያበላሽ መንገድ” እንደሚደረግ  ርዕሰ መስተዳድሩ በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል። የከተማ፣ ወረዳ እና ዞን አመራሮች “የመሬት ወረራ በሚመስል ሁኔታ ያለፕላን እና ዘርፍን ባልለየ መንገድ በየራሳቸው መሬት በማደል” የከተማውን ብቻ ሳይሆን የገጠሩንም ዕድገት የሚገታ ምሪት እንደሚሰጡም ዶ/ር ይልቃል በደብዳቤያቸው አትተዋል። 

“ህጉ ለሚፈቅድለትም ሆነ ለማይፈቅድለት አካል የመሬት ባለቤትነት ደብተር በማደል፤ በከተማ ዙሪያ ያለን መሬት የህገ ወጥ ወረራ ማካሄድ ይስተዋላል” ሲሉ በደብዳቤያቸው ያሰፈሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህ የሚከናወነውም “ከተማን እና የከተማ ዙሪያን ብቻ ያማለከ መሬትን በስጦታ በማስተላለፍ” መሆኑን አመልክተዋል። 

የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ፤ በከተሞች ዙሪያ የሚገኙ መሬቶች ተመራጭ የሆኑት “ለመስራት ሳይሆን፤ መሬት ላልተፈለገ ዓላማ ለማዋል ነው” ይላሉ። ለዚህም በምሳሌነት የሚጠቅሱት “በአንድ ዘርፍ ላይ የተሰጡ ፕሮጀክቶች፤ ሶስት አራት ጊዜ ዘርፋቸው ተቀይሮ” ማግኘታቸውን ነው። 

በከተሞች ዙሪያ የኢንቨስትመንት ስምሪት “በተዘበራረቀ ሁኔታ” የሚካሄድ መሆኑንም አቶ እንድሪስ በተጨማሪነት ያነሳሉ። “አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ እና ለኢንዱስትሪው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በሌሉበት ተተክለው ለመልካም አስተዳደር ችግር የሚሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል” የሚሉት የቢሮ ኃላፊው፤ በዚህ ምክንያት ለኢንዱስትሪዎቹ አስፈላጊው መሰረት ልማት ሊሟላ አለመቻሉን ይገልጻሉ።  

“ህጉ ለሚፈቅድለትም ሆነ ለማይፈቅድለት አካል የመሬት ባለቤትነት ደብተር በማደል፤ በከተማ ዙሪያ ያለን መሬት የህገ ወጥ ወረራ ማካሄድ ይስተዋላል”

ዶ/ር ይልቃል ከፋለ – የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

“እያንዳንዱ ወረዳ የራሱ አቅሞች አሉት። እዚያ ወረዳ ላይ የሚገባው ፕሮጀክት፤ ወረዳውን አቅም ባማከለ መልኩ መሆን አለበት” ሲሉ አቶ እንድሪስ በክልሉ ኢንቨስትመንት ሊመራበት ይገባል የሚሉት አካሄድ ጠቁመዋል። “የኢንቨስትመንት ልማቱ ይሄንን አሰራር ባልተከተለ መልኩ፤ በከተሞች ዙሪያ ባልተፈቀደ እና ስርዓት በሌለው መልኩ የሚሄድበት ሁኔታ ተፈጥሯል” የሚሉት የቢሮ ኃላፊው፤ እነዚህን ሁኔታዎች ማስተካከል የሚቻለው የኢንቨስትመንት ስምሪቱ “በተማከለ መልኩ ሲመራ ብቻ ነው” ሲሉ ክልሉ መፍትሔ ያለውን አሰራር ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)