“በትርጉም ስህተት” ተሰርዞ የነበረው የዕንባ ጠባቂ ተቋም ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች “ያለመከሰስ መብት”፤ በአዲስ የአዋጅ ማሻሻያ ላይ በድጋሚ ተካተተ 

በሃሚድ አወል

ለኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ተሿሚዎች፣ ዳይሬክተሮች እና መርማሪ ባለሙያዎች፤ ያለመከሰስ መብትን (immunity) በድጋሚ የሚሰጥ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ተመራ። ለተቋሙ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሰጥቶ የነበረው ይህ መብት በድጋሚ በአዋጅ እንዲካተት የተደረገው፤ የዛሬ አራት ዓመት የአዋጅ ማሻሻያ በተደረገበት ወቅት “በተሳሳተ ትርጉም” ምክንያት በመሰረዙ ነው ተብሏል። 

የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን ለማቋቋም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1992 ዓ.ም የወጣው አዋጅ፤ የተቋሙ ተሿሚዎች እና መርማሪዎች “ያለመከሰስ እና ያለመታሰር መብት” እንዳላቸው ይደነግግ ነበር። አዋጁ በ2011 ዓ.ም ሲሻሻል ግን ያለመከሰስ መብትን የሚያትተው ድንጋጌ ሳይካተት ቀርቷል።  

ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 13፤ 2015 ለፓርላማ የቀረበ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አዲስ የአዋጅ ማሻሻያ ማብራሪያ፤ ድንጋጌው ያልተካተተው “በተሳሳተ ትርጉም” ምክንያት ነው ብሏል። ማብራሪያው አክሎም “የቀደመው ምክር ቤት ለዕንባ ጠባቂዎች እና ለተቋሙ ከሚሰጠው ህገ መንግስታዊ ያለመከሰስ መብት ጋር በማነጻጸር፤ ከማሻሻያ አዋጁ በስህተት እንዲሰረዝ አድርጓል” ሲል ከዚህ በፊት ተፈጽሟል ያለውን “ስህተት” አብራርቷል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“ለዕንባ ጠባቂዎች እና መርማሪዎች የሚሰጠው ያለመከሰስ መብት፤ ፈጽሞ ለምክር ቤት አባላት ከሚሰጠው መብት ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን ታውቆ በዚህ አዋጅ ውስጥ በድጋሚ እንዲካተት ተደርጓል” ሲል የማሻሻያ አዋጅ ማብራሪያው አስረድቷል። በዚህም መሰረት በአዋጅ ረቂቁ በድጋሚ እንዲካተት የተደረገው አንቀጽ፤ “ማንኛውም የተቋሙ ተሿሚ፤ የተወካዮች ምክር ቤቱ ሳይፈቅድ ወይም ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር አይያዝም፣ አይከሰስም፣ አይታሰርም” ሲል ደንግጓል። 

በማሻሻያ አዋጁ መሰረት “ተሿሚ” የሚባሉት፤ ዋና ዕንባ ጠባቂውን ጨምሮ የተቋሙን አራት የኃላፊነት ቦታዎች የያዙ ናቸው። የተቋሙ ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ፤ የሴቶች፣ የህጻናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን ዕንባ ጠባቂ እንደዚሁም   የልዩ ልዩ ዘርፍ ዕንባ ጠባቂ፤ እንደ ዋና ዕንባ ጠባቂ ሁሉ በተወካዮች ምክር ቤት የሚሾሙ ኃላፊዎች ናቸው።   

ያለመከሰስ መብትን የደነገገው የአዋጅ ማሻሻያው አንቀጽ፤ ከተሿሚዎች በተጨማሪ በተቋሙ ላሉ ዳይሬክተር ጄነራሎች፣ ዳይሬክተሮች ወይም መርማሪዎች ተመሳሳይ ከለላ ይሰጣል። እነዚህ የተቋሙ ባለሙያዎች ሊያዙ፣ ሊከሰሱ አሊያም ሊታሰሩ የሚችሉት፤ ከዋና ዕንባ ጠባቂው ፈቃድ ከተገኘ ወይም ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ከተያዙ ብቻ እንደሆነ በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ሰፍሯል።

በአዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ፤ የዕንባ ጠባቂ ተቋሙ “በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደል አቤቱታዎችን መቀበል እና ምርመራ በማድረግ የመፍትሔ ሃሳብ የመስጠት” ስልጣን ተሰጥቶታል።

በስድስት ክፍሎች እና 47 አንቀጾች የተዘጋጀው የአዋጅ ረቂቁ፤ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች አራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይም ማሻሻያዎች አድርጓል። ማሻሻያ ከተደረገባቸው ውስጥ፤ የዕንባ ጠባቂ ተቋም ስልጣን እና ተግባራትን የሚዘረዝረው የአዋጁ ክፍል ይገኝበታል። 

በአዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ፤ የዕንባ ጠባቂ ተቋሙ “በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደል አቤቱታዎችን መቀበል እና ምርመራ በማድረግ የመፍትሔ ሃሳብ የመስጠት” ስልጣን ተሰጥቶታል። የተቋሙ የስልጣን ወሰን ወደ ግል ድርጅቶች እንዲሰፋ የተደረገው፤ ኢትዮጵያ ከምትከተለው “የነጻ ገበያ ስርዓት አንጻር ከመንግስት ሚና ይልቅ የግል ተቋማት በኢኮኖሚው የሚኖራቸው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ የማይቀር በመሆኑ ነው” ሲል ማብራሪያው አትቷል። 

በስራ ላይ ባለው የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት፤ የዕንባ ጠባቂ መስሪያ ቤት ያለው ስልጣን “በመንግስት አስፈጻሚ አካላት እና በመንግስት የልማት ድርጀቶች የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን መመርመር” ላይ የተወሰነ ነው። ተቋሙ ምርመራዎችን ካደረገ በኋላ ለሚመለከታቸው አካላት “ምክረ ሃሳብ” እንደሚያቀርብ በዚሁ አዋጅ ተደንግጓል።

በአዲሱ አዋጅ ማሻሻያ የተደረገበት ሌላው ጉዳይ፤ የተቋሙን ሰራተኞች ጥቅማ ጥቅም የሚመለከተው ነው። አሁን በሚሰራበት አዋጅ፤ የተቋሙ ሰራተኞች ጥቅማ ጥቅም የመወሰን ስልጣን ያለው የተወካዮች ምክር ቤት ነው። ይህ ስልጣን በአዲሱ አዋጅ፤ አራት አባላት ላሉት ለዕንባ ጠባቂዎች ጉባኤ ተላልፏል። የዕንባ ጠባቂዎች ጉባኤ የሚመራው በተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ነው። 

የተቋሙን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የሚመሩ ኃላፊዎች ሹመት፤ ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት የአዋጁ ክፍል ነው።   “የቅርንጫፍ ዕንባ ጠባቂ” የተሰኘ ስም እነዚህ ኃላፊዎች፤ ከዚህ ቀደም ይሾሙ የነበረው በተወካዮች ምክር ቤት ነበር። አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ ይህንን አካሄድ በመቀየር፤ ሹመቱ በዕንባ ጠባቂዎች ጉባኤ እንዲከናወን የሚወስን አንቀጽ አካትቷል። ሹመቱ የሚከናንወነ “በውድድር” እና “ብቃትን መሰረት ባደረገ” መልኩ እንደሚሆን የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ ሰፍሯል።

የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን ለሁለተኛ ጊዜ የሚያሻሽለው ይህ አዋጅ፤ በዝርዝር እንዲታይ ለፓርላማው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል። ይህንን የአዋጅ ማሻሻያ ለቋሚ ኮሚቴ የተመራው፤ በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በተገኙ 238 የፓርላማ አባላት “ሙሉ ድምጽ” ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)