የተወካዮች ምክር ቤት፤ ህወሓትን ከአሸባሪነት ለመሰረዝ የሚያስችል “ልዩ ጉባኤ” በነገው ዕለት ሊያካሄድ ነው 

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) ከአሸባሪነት ለመሰረዝ ነገ ረቡዕ መጋቢት 13፤ 2015 “ልዩ ጉባኤ” ሊያካሄድ መሆኑን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገለጹ። ሰባት የፓርላማ አባላት፤ ለነገው ልዩ ጉባኤ “ማንም አባል እንዳይቀር” ከሚል ማሳሰቢያ ጋር ጥሪ እንደተደረገላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

እነዚሁ የምክር ቤት አባላት በነገው ዕለት “ልዩ ጉባኤ” እንደሚካሄድ ቢያረጋግጡም፤ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር እንደሚደረገው የስብሰባው አጀንዳ አስቀድሞ እንዳልተላከላቸው አስታውቀዋል። የፓርላማ አባላቱ ይህን ቢሉም፣ የተወካዮች ምክር ቤት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ግን በነገው ስብሰባ ህወሓትን ከሽብርተኝነት የሚሰረዝ የውሳኔ ሃሳብ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።  

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብርተኝነት ስረዛውን የሚያካሄደው፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ከአምስት ወር ገደማ በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ነው። ባለፈው ጥቅምት ወር በተደረገው በዚሁ የሰላም ስምምነት፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት በህወሓት ላይ የተላለፈውን የአሸባሪነት  ውሳኔ ፍረጃ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር እንዲነሳ ያመቻቻል” የሚል አንቀጽ ተካትቷል።

የህወሓትን ከአሸባሪነት መሰረዝ በተመለከተ፤ የገዢው የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የፓርላማ አባላት ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 12፤ 2015 ውይይት ማድረጋቸውን የተወካዮች ምክር ቤት ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በፓርላማው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከረፋድ ሶስት ሰዓት ጀምሮ የተካሄደው ይህ ስብሰባ ለአምስት ሰዓታት የቆየ እንደነበር ምንጮቹ አክለዋል። 

በስብሰባው ላይ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እና በፓርላማ የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጅጌ መገኘታቸውን ምንጮች ገልጸዋል። በስብሰባው አብዛኛውን መድረክ ይዘው የቆዩት አቶ ሬድዋን፤ የህወሓት ከአሸባሪነት መነሳት ያለውን ፋይዳ ለፓርላማ አባላቱ አብራርተዋል ተብሏል። 

“የሰላም ስምምነት ሂደቱን ለማስቀጠል፤ የትግራይ ክልል በተሟላ ሁኔታ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲገባ እና በክልሉ ጊዜያዊ መንግስት እንዲቋቋም” ህወሓትን ከሽብርተኝነት መሰረዝ “አስፈላጊ” መሆኑን አቶ ሬድዋን ለአባላቱ መግለጻቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ ሬድዋን በዛሬው ስብሰባ ላይ፤ ህወሓት በአሸባሪነት የተፈረጀው “ለሀገር አደጋ ስለሆነ እንጂ፤ የህወሓትን አስተሳሰብ እና ሰዎች ስለምንጠላ አይደለም” ማለታቸውንም እነኚሁ ምንጮች አስታውቀዋል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን አሸባሪነት የፈረጀው፤ ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት በሚያዚያ 2013 ዓ.ም መጨረሻ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ላይ፤ ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራውን እና በመንግስት “ሸኔ” በሚል የሚታወቀው ታጣቂ ቡድንም በአሸባሪነት መፈረጁ ይታወሳል።

ሁለቱ አካላት በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ለፓርላማው የውሳኔ ሀሳብ የቀረበው በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተላለፈው ውሳኔ አማካኝነት ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህወሓት እና “ሸኔ” በሽብር እንዲፈረጁ ውሳኔ ባስተላለፈበት ስብሰባው፤ ሁለቱ አካላት “የሽብር ወንጀልን ዓላማቸው አድርገው” እንደሚንቀሳቀሱ እና “የሽብር ተግባር መፈጸም የድርጅቶቹ ጠቅላላ መገለጫ” መሆኑን ጠቅሶ ነበር። የሁለቱ ቡድኖች የስራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጪ አካላት፤ የሽብር ወንጀሉን “አምነው የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን እየመሩት” መሆኑንም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በወቅቱ ገልጿል። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ይህን ውሳኔ በመንተራስ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓት እና “ሸኔ” አሸባሪነት እንዲሰየሙ የወሰነው በአብላጫ ድምጽ ነበር። የሽብርተኝነት ፍረጃው እንዲጸድቅ ለተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት፤ ከአንድ የፓርላማ አባል ድምጸ ተዐቅቦ ገጥሞት ነበር።  

በዚህ አይነት አካሄድ በሽብርተኝነት የተፈረጀ ድርጅት ስያሜው እንዲሰረዝለት፤ “ማንኛውም ሰው ለፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ማመልከት እንደሚችል” በአዋጅ ተደንግጓል። የሽብር ወንጀልን ለመከላከል ለመቆጣጠር በ2012 ዓ.ም. የወጣው ይኸው አዋጅ፤ የፌደራል አቃቤ ህግ በአሸባሪነት ተሰይሞ ያለ ድርጅት ስያሜው እንዲሰረዝለት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ሊያቀርብ እንደሚችል ያትታል። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔውን ሲቀበለው፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በመቀበል ከአሸባሪነት ስያሜ ድርጅትን መሰረዝ ይችላል” ሲልም አዋጁ ቀጣይ ሂደቱ ምን እንደሚሆን አስቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]