በተስፋለም ወልደየስ
የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማካተቱ ውሳኔ፤ “ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን” ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ። ይህ ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይደረግ “ሆን ብለው የአፍራሽነት ሚና በሚጫወቱ” አካላት ላይ፤ “ተገቢው የህግ ማስከበር እርምጃ” እንደሚወሰድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያሉት፤ የክልል ልዩ ኃይሎችን በሚመለከት በመንግስት የተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ዛሬ እሁድ ሚያዝያ 1፤ 2015 በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው በተሰራጨ መግለጫቸው ነው። አብይ በዚሁ መግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ ከክልል ልዩ ኃይሎች ጋር በተያያዘ “ከአንዴም ሁለት ጊዜ የሀገርን ሉዓላዊነት እና አንድነትን የተገዳደሩ ፈተናዎች ገጥመዋት እንደነበር” ገልጸዋል።
አብይ የልዩ ኃይሎቹ መደራጀት ፈጥሮታል ካሉት “የአንድነት እና ሉዓላዊነት ስጋት” በተጨማሪ፤ “በክልሎች መካከል የማያስፈልግ ተፎካካሪነት እና ተገዳዳሪነት እንዲፈጠር መንስኤ” ሲሆን መታየቱን በመግለጫቸው ጠቁመዋል። በልዩ ኃይሎቹ መኖር ምክንያት “ከሕገ ወጥ የኬላ ዝርጋታ፣ ከኮንትሮባንድ እና ከሽፍትነት ጋር የተያያዙ ፈተናዎች” መስተዋላቸውንም አክለዋል።
በእነዚህ ምክንያቶችም፤ “ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅም ሲባል አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ተገቢ” መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት “ከዚህ በኋላ ክልሎች የፖሊስ ኃይላቸውን አጠናክረው፤ ወንጀልን በመከላከል እና አካባቢያዊ ጸጥታን በማስከበር ላይ ብቻ” እንዲያተኩሩ እንደሚደረግ አብይ አስታውቀዋል። “ከየትኛውም ኃይል የሚሰነዘር፣ የሀገርን ድንበር፣ ህልውና እና ሉዓላዊነት የሚዳፈር ኃይል ሲነሳ ደግሞ የመከላከያ ሰራዊቱ እርምጃ ይወስዳል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ይህንን ውሳኔ ለማስፈጸም የሚረዳ “አደረጃጀት በተግባር ላይ መዋሉን” አብይ በዛሬው መግለጫቸው አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታ ኃይሎች አዲስ አደረጃጀት እና አሰፋፈር እንደሚከተሉ፤ ከአንድ ሳምንት በፊት በፓርላማ በቀረቡበት ወቅትም ጥቆማ ሰጥተው ነበር። አብይ በወቅቱ “በስራ አስፈጻሚ በተገመገመው፣ በተወሰነው መሰረት፤ በሁሉም አካባቢ ያሉ ኃይሎች በሕገ መንግስቱ መሰረት በልካቸው እንዲሆኑ የተጀመረ ስራ አለ” ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የፓርላማ ንግግራቸው “ኮንትሮባንድን፣ ህገ ወጥ ትጥቅን፣ በየቦታው ሰው መግደል፣ መዝረፍን መከላከል በሚያስችል አሰፋፈር፤ የሀገር መከላከያ እና ፌደራል ፖሊስ አብዛኛውን critical ቀጠና በሚይዙበት መንገድ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ጅማሮ ውጤቶች ያታያሉ፡፡ ግን በሚቀጥሉት ወራት በበለጠ ይጠናከራል የሚል ተስፋ እና እምነት አለኝ፡፡ ኃይሉ ቦታ ቦታውን እየያዘ ሲሄድ፣ ከአንድ አካባቢ ከተሰበሰበበት ሲበተን፤ በድፍን ኢትዮጵያ ያሉ እንቅስቃሴዎች ለማስተካከል እድል ይሰጣል” ማለታቸው ይታወሳል።
አብይ ይህን በተናገሩ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፤ የክልል ልዩ ኃይሎች አባላትን “ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያደርግ “ተግባራዊ እንቅስቃሴ” መጀመሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል። የክልል ልዩ ኃይሎች አባላት እንደ የፍላጎታቸው ይገቡባቸዋል የተባሉት አደረጃጀቶች፣ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊስ የጸጥታ መዋቅሮች መሆናቸውንም የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ አስታውቋል።
የፌደራል መንግስት በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ ከማውጣቱ አስቀድሞ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ውሳኔውን በመቃወም መግለጫ አውጥቷል። የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያስተላለፈው ውሳኔ “የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት” መሆኑን ደርሼበታለሁ ያለው አብን፤ ይህም በሁሉም ክልሎች “በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ ይሆናል” የሚል እምነት እንደሌለው ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ጠቅሶ ነበር። ገዢው ፓርቲ ያስተላለፈው ውሳኔ “ወቅቱን ያልጠበቀ እና ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው” ሲል የተቸው ፓርቲው፤ ውሳኔው ተፈጻሚ ከሆነ የአማራ ህዝብን “ያለ ተከላካይ፣ ለዳግም ወረራ እና ጥቃት የሚዳርግ ነው” በማለትም ነቅፏል።
ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም፤ ትላንት ቅዳሜን ጨምሮ ባለፉት ቀናት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የአደባባይ ተቃውሞዎች ተደርገዋል። በደጀን ከተማ ከትላንት በስቲያ አርብ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች፤ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር የሚወስደውን አውራ ጎዳና ዘግተዋል። በዚሁ ተቃውሞ ወቅት ንብረትነቱ የፌደራል ፖሊስ የሆነ አንድ ተሽከርካሪ መቃጠሉም ተነግሯል። በከተማይቱ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በትላንትናው ዕለትም ቀጥሎ መዋሉን የደጀን ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ እሁድ ጠዋት በተሰራጨው መግለጫቸው፤ ተቃውሞ ከሚያነሱ አካላት ውስጥ የተወሰኑት ጉዳዩን በደንብ ካለመረዳት የሚያደርጉት መሆኑን ገልጸዋል። ቀሪዎቹ አካላት ግን “ሆን ብለው” ውሳኔውን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ናቸው ሲሉ ከስሰዋል። “ ‘የዚህ ወይም የዚያ ክልል ልዩ ኃይል ብቻውን ትጥቅ ሊፈታ ነው፤ የዚህኛው ክልል ይቆይ ተብሏል፤ ይሄን ወይም ያንን ሕዝብ ለመጉዳት የተደረገ ነው’ የሚሉ ውዥንብሮችን የሚነዙ አካላት፤ ገሚሶቹ ባለማወቅ ሲሆን፣ የተቀሩት ዓላማቸው ሕዝብ ከማበጣበጥ የዘለለ አይደለም” ብለዋል አብይ።
“ጥቂት የማይባሉት ‘የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ አለበት’ ብለው ሲጽፉና ሲሞግቱ የከረሙ ናቸው። ጠለቅ ብለን ብንፈትሻቸው፤ ‘ይሁን ሲሏቸው አይሁን፣ አይሁን ሲሏቸው ይሁን’ የማለት ልማድ የተጠናወታቸው ሆነው እናገኛቸዋለን” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ተችተዋል። አብይ “የአፍራሽነት ሚና” አላቸው ባሏቸው አካላት ላይ መንግስታቸው ሊወስደው ስላሰበው እርምጃም በመግለጫቸው ጥቆማ ሰጥተዋል።
“ሳይገባቸው የሚቃወሙትን ለማስረዳት እና ለማሳመን ጥረት እናደርጋለን። ሆን ብለው የአፍራሽነት ሚና በሚጫወቱት ላይ ደግሞ ተገቢው የሕግ ማስከበር እርምጃ ይወሰዳል። ለዚህም በቂ ዝግጅት ተደርጓል” በማለት አስጠንቅቀዋል። የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማካተቱ ውሳኔ፤ “ለኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እና ለሕዝቡ ሰላም ሲባል ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ተግባራዊ ይደረጋል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የመንግስታቸውን አቋም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)