በተስፋለም ወልደየስ
የኢትዮጵያ መንግስት ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራው “ኦነግ ሸኔ” ጋር የሚያደርገውን ድርድር፤ ከነገ በስቲያ ማክሰኞ ሚያዝያ 17፤ 2015 በታንዛንያ እንደሚጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ። በትግራይ ክልል የሰፈነውን “የሰላም ጅማሮ በተግባር ለማስቀጠል”፤ የሁሉም ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች በቀጣዮቹ ቀናት ወደ መቐለ እንደሚጓዙም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በተዘጋጀ የሽልማት እና የእውቅና መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። በአዲስ አበባው የወዳጅነት አደባባይ ዛሬ እሁድ ሚያዝያ 15፤ 2015 በተከናወነው በዚሁ መርሃ ግብር ላይ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓትን ወክለው በደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ የሰላም ንግግር ሲያደርጉ የነበሩ ልዑካን አባላት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በአፍሪካ ህብረት መሪነት ሲካሄድ የቆየውን የሰላም ንግግር በአመቻችነት ሲመሩ የቆዩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ “ልዩ ሽልማት” አግኝተዋል። ከኦባሳንጆ ጋር በሰላም ንግግሮቹ ላይ “በደጋፊነት” የተካፈሉት ቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፑምዚ ለምላምቦ የኢትዮጵያ ካርታን ከወይራ ዘንጣፊ ጋር በጋራ የያዘ ቅርጽን እና የዕውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

በሰላም ንግግሩ በታዛቢነት ሲሳተፉ የቆዩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሃና ቴት እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመርም ተመሳሳይ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። በዛሬው መርሃ ግብር ማብቂያ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ በቀጣይ ሳምንት ውስጥ ሁለት ኩነቶች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል። ከሁለቱ ክንውኖች ውስጥ አንደኛው የኢትዮጵያ መንግስት ከ“ኦነግ ሸኔ” ጋር የሚያደርገው ድርድርን የተመለከተ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል።
“ይህን ድርድር የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ አብዝቶ ይፈልገዋል። በዚህ ድርድር የሚሳተፉ ወገኖች ሁሉ የዛሬዋን ቀን እያሰቡ፤ ከግጭት፣ ከጦርነት እንደማናተርፍ አውቀው፤ ህግ እና ስርዓት ተከትለን፣ ይቅር ተባብለን፣ ሀገራችንን በጋራ ማነጽ እና መገንባት እንድንችል፤ የወለጋ ህዝብ አሁን ካለበት ስቃይ እፎይ ማለት እንዲችል፤ ሁሉም ወገን የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ከወዲሁ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው ንግግራቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ ከሚጠራው የ“ኦነግ ሸኔ” ቡድን ጋር “የሰላም ድርድር” ለማካሄድ፤ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ ያደረገው ባለፈው መጋቢት ወር ነበር። የፌደራል መንግስት ከ“ኦነግ ሸኔ” ጋር የሰላም ድርድር ለማካሄድ “ከአስር በላይ ሙከራዎች” አድርጎ እንደነበር መጋቢት 19፤ 2015 በነበረው የፓርላማ ውሎ ላይ መገለጹ ይታወሳል።
ይህንኑ ለፓርላማ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ የሰላም ድርድርን በተመለከተ መንግስት ከዚህ ቀደም ያደረጋቸው ሙከራዎች የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣታቸውን አስታውቀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙከራዎቹ ውጤት ያላመጡበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ “ያስቸገረው ነገር አንድ የተሰባሰበ ኃይል ባለመሆኑ፤ የምንነጋገርባቸው ኃይሎች የተለያዩ ሀሳብ እና አቋም ይዘው ስለሚመጡ ነው” ብለው ነበር።
ይህንን ተከትሎ “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ባወጣው መግለጫ፤ ከዚህ ቀደም የተደረጉት ሙከራዎች “የሰራዊቱን መኮንኖች እጅ እንዲሰጡ የማግባባት” ስራዎች እንደሆኑ በመጥቀስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገለጻ መተቸቱ አይዘነጋም። አማጺ ቡድኑ በዚሁ መግለጫው፤ ከፌደራል መንግስት ጋር በሚደረግ የሰላም ንግግር ላይ “ሶስተኛ ወገን” የሆኑ ዓለም አቀፍ አካላት እንዲሳተፉበት ከዚህ ቀደም ያቀረበውን ቅደመ ሁኔታ በድጋሚ አንስቶ ነበር።
ታጣቂ ቡድኑ ዓለም አቀፍ አካላት እንዲሳተፉ የፈለገው፤ “ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ዋስትና መስጠት” የሚችሉ አካላት ናቸው የሚል መከራከሪያን በማቅረብ ነው። “ተገቢው ገለልተኛ አለም አቀፍ የሶስተኛ ወገንን” ያሳተፈ የሰላም ንግግር ለማካሄድ፤ “አዎንታዊ ምልክቶች” እንዳሉ የመጋቢቱ የአማጺ ቡድኑ መግለጫ ጥቆማ ሰጥቶም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ንግግራቸው፤ ከ“ኦነግ ሸኔ” ጋር በታንዛንያ ይደረጋል በተባለው የሰላም ድርድር ላይ “ሶስተኛ ዓለም አቀፍ ወገን” ስለመሳተፉ ያሉት ነገር የለም።
አብይ በዚሁ ንግግራቸው ያነሱት ሌላኛው የቀጣዩ ሳምንት አበይት “ኩነት”፤ የሁሉም ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ወደ መቐለ ከተማ የሚያደረጉት ጉዞ ነው። ይህ ጉዞ የሚመራው በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል። ርዕሰ መስተዳድሮቹ የትግራይ ክልል መንግስት መቀመጫ ወደ ሆነችው መቐለ ከተማ የሚያቀኑት፤ “ያነቡ ዓይኖችን ለማበስ፤ የተበላሹ፣ የፈረሱ ቦታዎችን ለመጠገን” እንዲሁም “ክልሎች እንደ ወንድም ህዝቦች ካላቸው ለማጋራት” መሆኑን አብይ ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት ቀናት ይደረጋል የተባለው ይህ ጉዞ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን “የሰላም ጅማሮ በተግባር ለማስቀጠል” ያለመ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህ ጉዞ ሌሎች ክልሎች “የትግራይን ህዝብ ከጎኑ መሆናቸውን” የሚያሳዩበት መሆኑንም አብይ ጨምረው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል። የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሃሚድ አወል ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል።]