አቶ ግርማ የሺጥላን ጨምሮ አምስት ሰዎች በ“ኢ-መደበኛ ኃይሎች” መገደላቸውን የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ

በአማኑኤል ይልቃል

የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላን ጨምሮ አምስት ሰዎች በ“ኢ-መደበኛ ኃይሎች” በደረሰባቸው ጥቃት መገደላቸውን የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ። እነዚህ ኃይሎች በአቶ ግርማ ቤተሰቦች እና የግል ጥበቃዎቻቸው ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት፤ በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ጓሳ አካባቢ መሆኑንም የክልሉ መንግስት ገልጿል።

የአማራ ክልል መንግስት ይህንን ያስታወቀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአቶ ግርማን ሞት ይፋ ካደረጉ ከአንድ ሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአቶ ግርማ ሞት ተጠያቂ ያደረጉት፤ “ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ያቃታቸው” እንዲሁም “ነውጠኛ ጽንፈኞች” ሲሉ የገለጿቸውን አካላት ነው። የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ ጥቃቱን የፈጸሙት “ኢ-መደበኛ” እና “የሽብር ስራ እየሰሩ ያሉ ኃይሎች” ናቸው ብሏል።

የክልሉ መንግስት በዚሁ መግለጫው፤ አቶ ግርማ ጥቃት የደረሰባቸው ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 19፤ 2015 ከሰዓት በኋላ “የመንግስት እና የድርጅት ስራዎችን ሰርተው” ከመሃል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሃን እየተጓዙ በነበረበት ወቅት መሆኑን አስታውቋል። አቶ ግርማ የተወለዱት በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኘው መሃል ሜዳ አካባቢ መሆኑን የግል ህይወት ታሪካቸው ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዛሬ አመሻሽ ላይ ባወጡት መግለጫም፤ በአቶ ግርማ ላይ የተደረገው “አስነዋሪ እና አሰቃቂ ተግባር” የተፈጸመው፤ ተወልደው ባደጉበት አካባቢ እንደነበር ጠቅሰዋል።

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ከመገደላቸው አንድ ቀን አስቀድሞ፤ በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማ የስራ ጉብኝት ማካሄዳቸው ተገልጾ ነበር። የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በትላንትናው ዕለት ባወጣው መረጃ፤ አቶ ግርማ ከከተማዋ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ እና ከሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን መመልከታቸውን በፎቶግራፍ አስደግፎ አሳይቶ ነበር።

አቶ ግርማ እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ በአማራ ክልል መንግስት እና በክልሉ ገዢ ፓርቲ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ለ27 ዓመታት አገልግለዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ በመሆን በታህሳስ 1988 ዓ.ም የአመራርነት ስራን የጀመሩት አቶ ግርማ፤ በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመዋል። በዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይም ለሰባት ዓመት ገደማ ቆይተዋል።

በጥር 1995 ዓ.ም. ከወረዳ ወደ ዞን በመሸጋገርም፤ የቀድሞው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሰሜን ሸዋ ዞን ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ መሆን ችለዋል። ለአንድ ዓመት ገደማ በዚህ ኃላፊነት ቦታ የቆዩት አቶ ግርማ፤ በጥር 1996 ዓ.ም የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሹመት አግኝተዋል። 

እስከ መጋቢት 1998 ዓ.ም. በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ውስጥ በነበራቸው የኃላፊነት ቆይታ፤ የከተማዋ ማስታወቂያ፣ ወጣት ስፖርት ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳዩች ጽህፈት ቤቶችን ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ የደብረ ብርሃን ከተማ የፓርቲ ጽህፈት ቤትንም ሲመሩ ቆይተዋል። ከሚያዝያ 1998 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ዓመት ገደማ በቆዩበት በሰሜን ሸዋ ዞን ባሶና ወራና ወረዳ ደግሞ የማስታወቂያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል።

በ2002 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከደብረብሃን ዩኒቨርስቲ በምጣኔ ሃብት (ኢኮኖሚክስ) ትምህርት ዘርፍ ያገኙት አቶ ግርማ፤ በዚያው ዓመት የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ሆነዋል። እስከ ግንቦት 2003 ዓ.ም ድረስ በዚሁ ቦታ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፤ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመዋል። 

በምክትል አስተዳዳሪነት ደረጃ ለአራት ዓመታት ገደማ የቆዩት አቶ ግርማ፣ ዞኑን የመምራት ኃላፊነት በመስከረም 2008 ዓ.ም ተረክበዋል። የሰሜን ሸዋ ዞንን ለሁለት ዓመት ገደማ የመሩት አቶ ግርማ፤ በ2012 ዓ.ም በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኘው የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ይዘዋል።

የአቶ ግርማ ቀጣይ መዳረሻ የሆነው የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ነው። በህዳር 2013 ዓ.ም. ወር ቢሮውን በኃላፊነት እንዲመሩ የተሹሙት አቶ ግርማ፤ ሹመታቸው ከአራት ወራት በኋላ በክልሉ ምክር ቤት ጸድቋል። በዚያው ዓመት በተካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ፤ በባሶና ወረና ወረዳ ቀይት ምርጫ ክልል ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ለአማራ ክልል ምክር ቤት ተመርጠዋል።

አቶ ግርማ እስከ እለተ ሞታቸው በኃላፊነት በሰሩበት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የተሾሙት፤ ብልጽግና ፓርቲ ምርጫውን አሸንፎ የክልሉን መንግስት በመሰረተበት መስከረም 2014 ዓ.ም ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]