የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን አሰልጥኖ ወደ ውጭ ሀገር ለስራ ለማሰማራት እንቅስቃሴ መጀመሩን የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ

በሃሚድ አወል

የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን አሰልጥኖ ወደ ውጭ ሀገር ለስራ ለማሰማራት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ  ባለፉት ዘጠኝ ወራት 85 ሺህ ዜጎችን ወደ ውጭ ሀገር ለስራ ለማሰማራት አቅዶ ማከናወን የቻለው 66 በመቶ ብቻ ነው ብሏል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ስድስት ሚሊዮን ዜጎች በስራ ፈላጊነት መመዘገባቸውንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን የገለጸው ትላንት ሐሙስ ሚያዝያ 19፤ 2015 የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ነው። የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ በስራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና እንዲሁም በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ላይ መስሪያ ቤታቸው ያከናወናቸውን ስራዎች ለፓርላማው አብራርተዋል። 

የሚኒስትሯን ሪፖርት ተከትሎ ጥያቄዎችን ከሰነዘሩ የፓርላማ አባላት አንዱ የሆኑት አቶ ዮሃንስ መስፍን፤ “የውጭ ሀገር የስራ አማራጮችን ተጠቅሞ ለዜጎች ብቁ ስራ ዕድል ለመፍጠር ምን ታስቧል?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የአሰሪ እና ሰራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ አሰግድ ጌታቸው ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ከውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ጋር በተያያዘ የመዳረሻ ሀገራትን ለማበራከት ጥናት መጀመሩን ተናግረዋል።

“ከአረብ ሀገራት እና ከሌሎች የጎረቤት ሀገራት በተጨማሪ በአውሮፓም፣ በሰሜን አሜሪካም የስራ ዕድሎችን የማየት እና ጥናት ማጥናት ስራ እየሰራን ነው” ሲሉ ኢትዮጵያውያን ስራ ፈላጊዎችን ወደተለያዩ አህጉራት ለመላክ መታሰቡን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል። “እስካሁን የምንልከው በብዛት የቤት ሰራተኞችን እና በከፊል የሰለጠኑ ሙያተኞች ብቻ ነው” ያሉት አቶ አሰግድ፤ ይህንን አካሄድ በማስፋት የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ጭምር በማሰልጠን ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

ሚኒስቴር ዲኤታው “ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ወጣቶችን በመዳረሻ ሀገራት ባለው ገበያ መሰረት ለዚያ ሀገር ብቁ የሚያደርጋቸውን ስልጠናዎች በመስጠት ወደዚያ ሀገር ለማሰማራት ሰፊ እየተሰራ ነው” ሲሉ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲ ምሩቃኑን ለማሰልጠን 99 ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች መለየታቸውን ያነሱት አቶ አሰግድ፤ ለእነዚህ የትምህርት ተቋማት ቁሳቁስ እና ግብዓት የማሟላት ስራ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል። 

በትላንቱ የፓርላማ ስብሰባ በጥያቄ መልክ የተነሳው ሌላው ጉዳይ፤ የስራ አጥነት እና የስራ ዕድል ፈጠራን የተመለከተ ነው። ሙፈሪያት ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት በንባብ ባሰሙት ሪፖርት ላይ፤ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለ3.2 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ2.4 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል። ይህም በእቅድ ከተያዘው 79 በመቶውን ብቻ ያሳካ መሆኑንም ጠቁመዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደ ውጭ ለመላክ አቅዶ ከነበረው 85 ሺህ የስራ ፈላጊዎች ውስጥ ማሳካት የቻለው የዕቅዱን 66 በመቶ መሆኑንም አመልክተዋል። 

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀጥታ ስርጭት የተወሰደ

የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በስራ ፈጠራም ሆነ የስራ ፈላጊዎችን ወደ ውጭ በመላክ ረገድ ያከናወናቸውን ተግባራት በቁጥር አስደግፎ ቢያቀርብም፤ የፓርላማ አባላቱ ግን በተመረጡባቸው አካባቢዎች እና በአጠቃላይ “ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር” እንደሚስተዋል ተናግረዋል። “የስራ አጥ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው” ያሉት መዓዛ አስማረ የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ ቁጥሩን ለመቀነስ ምን እየተሰራ እንደሆነ ጥያቄ አቅርበዋል። 

መቅደስ ደስታ የተባሉ ሌላ የፓርላማ አባልም የስራ አጥነት ችግር በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የሚታይ መሆኑን በተመሳሳይ አንስተዋል። እርሳቸው በተመረጡበት በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን “ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር” መኖሩን ያነሱት መቅደስ፤ የዞኑ አስተዳደር “ችግሩን በራሱ አቅም ብቻ ለመፍታት አዳጋች ሆኖበታል” ብለዋል። ችግሩን ለመፍታት “የፌደራል መንግስቱን ወይም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የተለየ ጣልቃ ገብነት የሚፈልግ ነው” ያሉት የፓርላማ አባሏ፤ ሚኒስቴሩ “የተለየ ድጋፍ ለማድረግ ያቀደው ነገር አለ ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል። 

ለጥያቄዎቹ ምላሽ ሰጡት ሙፈሪያት ካሚል፤ “መንግስት ዋነኛ ስራ ፈጣሪ አይደለም። ዋነኛ ስራ ፈጣሪ የግሉ ዘርፉ ነው። የመንግስት ሚና ለግል ሴክተሩ የተመቸ ሁኔታ መፍጠር ነው” ብለዋል። ይህን የሚኒስትሯን ምላሽ ያስተጋቡት የስራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ የወላይታ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው የወላይታ ሶዶ ከተማ “ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር ካለባቸው” በሚል ከተለዩ 11 ከተሞች ውስጥ አንዷ መሆኗን ጠቁመዋል። በከተማይቱ ያለውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍም፤ መስሪያ ቤታቸው እያከናወነው ባለው “የስራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት” እንድትታቀፍ ማድረጉንም አስረድተዋል። 

የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፈጠራቸው ቋሚ የስራ ዕድሎች፤ የአካል ጉዳተኞች ድርሻ 0.35 በመቶ ብቻ መሆኑም በትላንቱ የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ጥያቄን አስነስቷል። ሚኒስትር ሙፈሪያት ለዚህ ጥያቄ በሰጡት መልስ “አካል ጉዳተኝት በእኛ ነባራዊ ሁኔታ አለመቻል ተደርጎ ስለሚወሰድ ብዙ የሚያበረታታ እና የሚያደፋፍር አይደለም” ሲሉ ችግሩ ከአስተሳሰብ ጋር ጭምር የሚያያዝ መሆኑን አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)