በሃሚድ አወል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፤ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፊት በክልሉ ተጀምረው በስራ ላይ የነበሩ ፕሮጀክቶች ውል እንዲታደስ ወሰነ። በጊዜያዊ አስተዳደሩ ቅድሚያ የማይሰጣቸው ፕሮጀክቶች ሊሰረዙ እንደሚችሉ የክልሉ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፤ የፕሮጀክቶች ውል “በጥናት መሰረት” እንዲታደስ ውሳኔ ያሳለፈው ትላንት ሐሙስ ሰኔ 29፤ 2015 ባካሄደው ስብሰባ ነው። “ውሎቹ የጊዜ ገደብ አላቸው፤ የዋጋ ልዩነት አለ። ስለዚህ [ፕሮጀክቶቹን] አሁን ባለው ሁኔታ እንዴት ማስቀጠል እንችላለን የሚለውን ነው የወሰንነው” ሲሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ገብረጻዲቅ የካቢኔውን ውሳኔ ዋና ጭብጥ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
በክልሉ የሚሰሩ እና ለማህበራዊ አገልግሎት የሚውሉ ፕሮጀክቶች፤ በውሳኔው መሰረት በቅደም ተከተል ተለይተው እንደሚቀመጡ ኃላፊዋ ገልጸዋል። “አሁን ባለንበት ሁኔታ የእያንዳንዱ ፕሮጀክት priority እየተቀመጠ፤ የማያስፈልግ ከሆነ ሊሰረዝም ይችላል” ያሉት ወይዘሮ አልማዝ፤ ይህ የተደረገበት ምክንያትም ክልሉ ያለውን በጀት መሰረት በማድረግ በቅደም ተከተል ማስቀመጥ በማስፈልጉ ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።
በትግራይ ክልል ግንባታቸው የሚቀጥሉ ፕሮጀክቶች አስፈላጊነታቸውን መሰረት በማድረግ የቅደም ተከተል ደረጃቸው የሚለየው፤ በክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች አማካኝነት መሆኑን የቢሮ ኃላፊዋ ጠቁመዋል። “የውሃ ፕሮጀክቶች በውሃ ሴክተር ይጠናሉ። የህንጻ ፕሮጀክቶች ከሆኑ በእኛ ይጠናሉ። የመንገድ ከሆኑ ደግሞ በመንገድ ሴክተር ይጠናሉ” ሲሉም የክልሉ መስሪያ ቤቶች በሚሰሩባቸው ዘርፎች ስር ያሉ ፕሮጀክቶችን በመከፋፈል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ለመለየት ስራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት ያህል ከተካሄደው ጦርነት በፊት ተጀምረው የነበሩ ፕሮጀክቶችን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ ቢያሳልፍም፤ ፕሮጀክቶቹ ወደ ግንባታ የሚመለሱት ግን “በጀት ሲገኝ” መሆኑ ተገልጿል። ፕሮጀክቶቹ እንደገና የሚጀመሩት “በጀት ስናገኝ ነው እንጂ፤ አሁን እኛ በጀት የለንም” ሲሉ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊዋ በክልሉ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስረድተዋል።
ከጦርነቱ በፊት በክልሉ ሲሰሩ ከነበሩት ፕሮጀክቶች ለተወሰኑት በጀት ይመደብ የነበረው፤ በትግራይ ክልል እንዲሁም በከተሞች እና በወረዳ አስተዳደሮች አማካኝነት እንደነበር ወይዘሮ አልማዝ አስታውሰዋል። “ከተሞች አሁን ግብር መሰብሰብ ስለጀመሩ በራሳቸው በጀት ፕሮጀክቶች ማስቀጠል ይችላሉ” ሲሉ የቢሮ ኃላፊዋ አክለዋል።
የፌደራል መንግስት በሚመደበው በጀት ግንባታቸው ሲከናወን የቆዩ ፕሮጀክቶች እንደነበሩም ገልጸዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ምንጫቸው የፌደራል መንግስት ይሁን እንጂ፤ ግንባታውን የሚያከናውኑት ድርጅቶች የውል ስምምነት ይፈጽሙ የነበረው ግን ከትግራይ ክልል አስተዳደር ጋር እንደሆነም ጠቁመዋል። ነገ ቅዳሜ ሐምሌ 1 ለሚጀምረው ለ2016 በጀት ዓመት፤ የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል በበጀት ድጎማ መልክ ለመስጠት ያጸደቀው የገንዘብ መጠን 12.5 ቢሊዮን ብር ነው።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ የትላንቱን ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት፤ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ከፌደራል መንግስት ጋር “የጋራ ምክክር” መደረጉን ወይዘሮ አልማዝ ጠቅሰዋል። የካቢኔው አባል የሆኑት ቢሮ ኃላፊዋ አክለውም፤ “እያሰብነው ያለነውን ነገር ነግረናቸዋል። በእሱ ሂዱና እናንተ የደረሳችሁበትን ስምምነት ለእኛ ላኩልን ብለዋል” ሲሉ ቀጣዩ ሂደት የትላንቱን ውሳኔ ዝርዝር ለፌደራል መንግስት መላክ እንደሆነ አስረድተዋል።
በትላንቱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ስብሰባ፤ ለፕሮጀክቶች ስለሚመደበው በጀት እና ለግንባታዎች ቅደም ተከተል መስጠት ማስፈለጉን በተመለከተ ከተላለፈው ውሳኔ በተጨማሪ የኮንትራክተሮች ጉዳይ መነሳቱንም የክልሉ ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ከትግራይ ክልል ጋር ውሎችን ፈጽመው ግንባታ ሲያከናውኑ የቆዩ ኮንትራክተሮች እንደሌላው ዘርፍ ሁሉ ጉዳት እንደደረሰባቸው ወይዘሮ አልማዝ ገልጸዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የኮንትራክተሮቹ ሰርተፍኬት ለሶስት ዓመት ያህል እንዳልታደሰ ያስታወሱት የቢሮ ኃላፊዋ፤ እድሳቱ እንዲሰጣቸው በትላንቱ ስብሰባ መወሰኑን ተናግረዋል። እድሳቱን ለማከናወንም “የአንድ ዓመት እድል እንዲሰጣቸው” ውሳኔ መተላለፉንም አስረድተዋል። ሰርተፍኬታቸው በፌደራል ደረጃ መታደስ ያለበትን ኮንትራክተሮችን ደግሞ፤ “ያለ ቅጣት እንዲታደስላቸው እና ሌላ የሚጠቀሙበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው” የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጉዳያቸውን ወደ ፌደራል ለማቅረብ መወሰኑን አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)