በአማራ ክልል “እርስ በእርስ በመገዳደል ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ ኪሳራ እያጋጠመ ነው” – ዶ/ር ይልቃል ከፋለ 

በአማኑኤል ይልቃል

በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት “እርስ በእርስ በመገዳደል ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ ኪሳራ” እያጋጠመ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ። ዶ/ር ይልቃል በክልሉ “በየአካባቢው” ይፈጸማል ያሉት “ትንኮሳ በአስቸኳይ እንዲቆም” እና የድርጊቱ ተሳታፊዎች  ወደ “ሰላማዊ ውይይት እንዲመለሱ” ጥሪ አቅርበዋል። 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይህንን የተናገሩት የክልሉን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 26፤ 2015 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። መንግስት የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ስራ ከጀመረ ወዲህ በአማራ ክልል ስለተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ በመግለጫቸው ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ የጸጥታ መዋቅር እና የመከላከያ ሰራዊት “ህግ ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ” መሆኑን ገልጸዋል። 

ለመከላከያ ሰራዊቱ “ያልተገባ ስም በመስጠት መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ እየተነዛ ነው” ያሉት ዶ/ር ይልቃል፤ የአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅር እና የመከላከያ ሰራዊት በየአካባቢው ሲንቀሳቀስ “መተንኮስ ተገቢም፤ ህጋዊም አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል። በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ተፈጽሟል የተባለው “ትንኮሳ”፤ ትላንት ማክሰኞ ሐምሌ 25፤ 2015 መግለጫ በሰጡት የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነም ተነስቶ ነበር።

ኮሎኔል ጌትነት በዚሁ መግለጫቸው፤ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ሁለት ጊዜ በሰራዊቱ ላይ ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር ተናግረዋል። የመጀመሪያው ተኩስ የተከፈተው የሰራዊቱ የሰሜን ምዕራብ እዝ አባላት፤ ጎርጎራ ፕሮጀክትን ለመጎብኘት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ  ከጯሂት ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት “ሰመረች” የምትባል አዲስ ቤተክርስቲያን አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ “ከፍተኛ ቦታና ገዢ ቦታ ነው ብለው ባሰቡት ወደ ሰራዊቱ ተኩሰው ነበር” ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ በሚመለሱበት ወቅት ደግሞ ቆላድባ፣ ወደ አዘዞ መውጫ፣ ድንጋይ መፍጫ በሚባለው አካባቢ “ተኩስ ለመክፈት ሙከራ” መደረጉን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። የመከላከያ ሰራዊቱ “በገጠመው ውጊያ ልክ እንደሚገጥም”   ኮሎኔል ጌትነት አስጠንቅቀዋል።

በአማራ ክልል “ጥቃት ተፈጽሞበታል” ከተባለው የመከላከያ ሰራዊት በተጨማሪ፤ የክልሉ የጸጥታ መዋቅርም ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠመው ዶ/ር ይልቃል በዛሬው መግለጫቸው ጠቁመዋል። በክልሉ በጸጥታ መዋቅሩ እንዲሁም በነዋሪው ላይ “እርስ በእርስ መገዳደል” እየተስተዋለ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህ ድርጊት እያስከተለ ያለው “ሰብአዊ ኪሳራ ከፍተኛ” እንደሆነም ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዛሬው መግለጫቸው በአማራ ክልል ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በሰላማዊ መንገድ ካልተፈታ “ክልሉን የበለጠ አደጋ ላይ የሚጥል” መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህ ችግር “እየዋለ እያደረ ሲሄድ ክልላዊ አለመረጋጋት፣ ስርዓት አልበኝነት እንዲሁም መሰረታዊ ሸቀጦች እና የህክምና ግብአቶች የሚያስተጓጉል እና የሚያቆም” ሊሆን እንደሚችልም ስጋታቸውን አንጸባርቀዋል።

ይህ ስጋት በእውን ከመከሰቱ አስቀድሞ “በየአካባቢው” የሚፈጠረው “ትንኮሳ እንዲቆም” በመግለጫቸው ያሳሰቡት ዶ/ር ይልቃል፤ ሁሉም አካላት “በሰላማዊ ውይይት ላይ እንዲሳተፉ” ጥሪ አቅርበዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ጥሪ ከአንድ ሳምንት በፊት በተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ አቅርበው ነበር። ዶ/ር ይልቃል በዚሁ ጉባኤ ላይ ያቀረቡት ጥሪ፤ የክልሉ ምክር ቤቱ አባላት በየዞናቸው ከታጣቂዎች ጋር የሰላም ንግግር እንዲያስጀምሩ የጠየቀ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)