የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ ከአማራ ክልል በተጨማሪ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም “እንዳስፈላጊነቱ” ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገለጸ

በተስፋለም ወልደየስ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ከአማራ ክልል በተጨማሪ እንዳስፈላጊነቱ “በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው” ተገለጸ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወር ጸንቶ ይቆያል ተብሏል። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ አርብ ሐምሌ 28፤ 2015 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የወሰነው፤ በአማራ ክልል ይታያል ያለውን “በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ”፤ “በመደበኛ የህግ ማስክበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ አስታውቆ ነበር። በዚህም ምክንያት “የህዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ” እንዲሁም “ህግ እና ስርዓት ለማስከበር” የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ መታወጁን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ገልጿል። 

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ምሽት ይፋ ያደረገው የድንጋጌው ዝርዝር፤ የአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን “በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር እንዲሁም በክልሉ አስተዳደር የህዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር የሚወሰድ እርምጃን” የሚያካትት መሆኑን አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ አዋጁ “በክልሉ ወይም በሃገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የጸጥታ ችግር የሚያባብስ ማንኛውም እንቅስቃሴ ወይም ሁኔታን በሚመለከት እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው” በድንጋጌው ላይ ሰፍሯል።

በአራት ክፍሎች እና በአስራ አንድ አንቀጾች የተከፋፈለው አዋጁ፤ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ መቋቋምና ኃላፊነት፣ አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት የስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የሚወሰዱ እርምጃዎች እና የተከለከሉ ተግባራት እንዲሁም ሌሎችም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን በዝርዝር አስፍሯል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው ጠቅላይ መመሪያ ዕዝ፤ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል የሚመራ መሆኑ አዋጁ አመልክቷል።

ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነው ይኸው ጠቅላይ መመሪያ ዕዝ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተፈጻሚ የሚያደርጉ ግብረ ኃይሎችን ወይም ኮሚቴዎችን ሊያቋቁም እንደሚችል ተደንግጓል። ጠቅላይ መመሪያ ዕዝ በአዋጁ የተዘረዘሩ እርምጃዎችን በተመለከተ “አስፈላጊውን ውሳኔ የማስተላለፍ እና የማስፈጸም” ስልጣን በአዋጁ ተሰጥቶታል። በአማራ ክልል መንግስት ስር የሚገኙ የህግ አስከባሪ አካላትን “በአንድ ዕዝ ስር አድርጎ በበላይነት የማስተባበር እና የመምራት” ተጨማሪ ስልጣን የተሰጠው ይህ አካል፤ በአዋጁ የተከለከሉ ተግባራት እና ግዴታዎችን የማስከበር ኃላፊነትም ተጥሎበታል።

“የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ” በሚል በዛሬው ዕለት ባወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የሚወሰዱ እርምጃዎች እና የተከለከሉ ተግባራት ተዘርዝረዋል። በአዋጁ መሰረት “ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ውጭ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ” የተከለከለ ነው።

በአማራ ክልል “የአመጽ እንቅስቃሴን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር እንዲሁም የጸጥታ መደፍረሱን የሚያባብስ ንግግር፣ የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ ቅስቀሳ በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጨት” መከልከሉም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙን “እንቅስቃሴ” እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን “አላማ የሚቃረን እና የሚቃወም” ንግግር ወይም የቅስቀሳ በተመሳሳይ ክልከላ ተደርጎበታል።

ለታጣቂ ቡድኖች “በየትኛውም መንገድ” “የገንዘብ፣ የመረጃ፣ የቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማድረግ” መከልከሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌ ላይ ተቀምጧል። ማንኛውንም ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ዘርፍም ሆነ በምርት ሂደት ላይ “የስራ ማስተጓጎል ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈጸም” እንደማይቻልም በአዋጁ ተደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]