አቶ ታዬ ደንደአ “ለጥፋት ተልዕኮ በህቡዕ ሲሰሩ ነበር” በሚል ተወንጅለው በቁጥጥር ስር ዋሉ

በትላንትናው ዕለት ከስልጣናቸው የተነሱት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በመተሳሰር ለጥፋት ተልዕኮ በህቡዕ ሲሰሩ ነበር” በሚል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። አቶ ታዬ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸሙ በቆዩ “የሽብር ተግባራት” በተለይም በእገታዎች ላይ “እጃቸው አለበት” ሲል ግብረ ኃይሉ ወንጅሏል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ሲሰሩ የቆዩት አቶ ታዬ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተጻፈ ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ትላንት ሰኞ ታህሳስ 1፤ 2016 ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ሚኒስትር ዴኤታው ከስልጣናቸው የተነሱበትን ምክንያት ባይጠቅስም፤ ይህንኑ ተከትሎ አቶ ታዬ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባወጡት ጹሁፍ ግን ከስልጣናቸውን የተነሱት “የወንድማማቾች መገዳደል ይቆም ዘንድ ለሰላም በመወገናቸው” መሆኑን አስፍረው ነበር። 

በኢትዮጵያ “በሀገር ህልውና ስም ሲካሄድ ነበር” ያሉትን ጦርነት “ኢትዮጵያውያንን ከማገዳደል አልፎ ሀገሪቷን ያደቀቃት” መሆኑን በጹሁፋቸው የገለጹት አቶ ታዬ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን “በሰዉ ደም የሚጫወቱ አረመኔ” ሲሉ ወርፈዋቸዋል። የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ በዛሬው መግለጫው፤ አቶ ታዬ በተመደቡበት ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ላይ ሆነው መንግስትን “ገዳይ እና ጨፍጫፊ” እያሉ “በተደጋጋሚ ሲወቅሱ” መደመጣቸውን ጠቅሷል። 

ሆኖም በተግባር “ከሽብርተኞች፣ ጽንፈኞች እና ነፍሰ ገዳዮች ጋር” በተግባር “የጥፋት ትስስር የነበራቸው” ራሳቸው አቶ ታዬ መሆናቸውን “በተደረገ ክትትል መረጋገጡን” የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አስታውቋል። የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን ተቀብለው እየሰሩ ባሉበት ወቅት “መንግስታዊ እና የፓርቲ መዋቅሩን በሴራ ለመናድ በህቡዕ  እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል” ሲል የሚከስሰው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ፤ ይህንኑ በመረዳትም በአቶ ታዬ ላይ “ያላሰለሰ ጥናት እና ክትትል ሲደረግባቸው እንደነበር” አትቷል።

በተደረገው ክትትልም አቶ ታዬ “ከኦነግ ሸኔ አመራሮች እና በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር” መንግስትን “በአመጽ፣ በሽብር እና በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል” ሲል የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው ወንጅሏል። አቶ ታዬ በህግ ቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት “በህቡዕ ለሚያደርጉት ጸረ-ሰላም እንቅስቃሴ ሲገለገሉባቸው ነበር” የተባሉ “ሞባይሎች፣ ላፕቶፖች፣ አይፖዶች፣ ፍላሾች፣ የተለያዩ ተሽከርካሪ ሰሌዳዎች” በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ “ፍተሻ” መገኘታቸውን መግለጫው አመልክቷል። 

በዚሁ ፍተሻ “ክላሽንኮቭ ጠመንጃ እና ሽጉጦች” “ከመሰል ጥይቶች ጋር” መገኘታቸውን ያስታወቀው የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ “የኦነግ ሸኔ አርማዎች” እና በተለያዩ ግለሰቦች ስም የተዘጋጁ “የኦነግ ሸኔ መታወቂያዎች፣ ሰነዶች እና ማስታወሻዎች” መያዛቸውንም ገልጿል። በአቶ ታዬ መኖሪያ ቤት በተደረገው ፍተሻ ወቅት፤ “የኦነግ ሸኔ አባል ነው” የተባለ ግለሰብ “ተደብቆ መገኘቱን” በቁጥጥር ስር መዋሉን የጋራ ግብረ ኃይሉ አክሏል።

የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ “በሕግ ሊያስጠይቃቸው የሚችል ነገር ይኖር እንደሆነ” በትላንትናው ዕለት ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ “ሕግ የታለና በሕግ ይጠይቁኛል። ከጠየቁኝ ደግሞ ዝግጁ ነኝ”ብለው ነበር። አቶ ታዬ “ኢትዮ ፎረም” ከተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም ተመሳሳይ ሃሳብ አስተጋብተዋል። 

“ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ነበሩ። እኔ የመጣሁት ‘ለመኪናም አይደለም፣ ለወንበርም አይደለም’ ብዬ [ለጠቅላይ ሚኒስትሩ] ነግሬዋለሁ። ስለዚህ የፈለገው ነገር ቢመጣ ዝግጁ ነኝ” ሲሉ አቶ ታዬ ለ“ኢትዮ ፎረም” ተናግረዋል። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘የሚያወጣ፣ የሚያሻግር መንገድ ይዟል’ ብዬ ባመንኩ ጊዜ ይህንን ለማሳመን ህይወቴን አስዤ ጭምር ሰርቼያለሁ። አሁን ደግሞ በጊዜ ሂደት ያ ነገር በዚያ መንገድ አለመሆኑን ስረዳ ያኔ የተሳሳተውን ህዝብ ለማስረዳት የሞራል ግዴታ አለብኝ” ሲሉም በቃለ ምልልሱ ተደምጠዋል።

የእርሳቸው አይነት አቋም በሌሎች ሚኒስትሮች እና ባለስልጣናትም ዘንድ ያስተውሉ እንደሆነ በ“ኢትዮ ፎረም” የተጠየቁት አቶ ታዬ፤ “በጣም ብዙ ሰው ብዙ ነገር መበላሸቱን እያየ ለመወሰን የተቸገረ እንዳለ አውቃለሁ። ግን ጉዳዩ ውሎ አድሮ የሚታይ ነው የሚሆነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተው ነበር። የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በዛሬው መግለጫው ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

“ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ነበሩ። እኔ የመጣሁት ‘ለመኪናም አይደለም፣ ለወንበርም አይደለም’ ብዬ [ለጠቅላይ ሚኒስትሩ] ነግሬዋለሁ። ስለዚህ የፈለገው ነገር ቢመጣ ዝግጁ ነኝ”

– አቶ ታዬ ደንደአ ለ“ኢትዮ ፎረም” መገናኛ ብዙሃን ከተናገሩት የተወሰደ

የጋራ ግብረ ኃይሉ በመንግስት እና በገዢው ፓርቲ መዋቅር ዉስጥ ሆነው በተመሳሳይ መልኩ “ለእኩይ ዓላማ” ተሰማርተዋል ባላቸው አካላት ላይ “በጥናት የተመሰረተ ጥብቅ ክትትል እያደረገባቸዉ እንደሚገኝ” ገልጿል። በእነዚሁ አካላት ላይ “እንደአስፈላጊነቱ የሚወሰዱ ህጋዊ እርምጃዎችን” በተከታታይ ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]