በ2023 ብቻ 50 የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች “ላልተገባ እስር መዳረጋቸው” ተገለጸ

በመገባደድ ላይ ባለው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት ብቻ 50 የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች “ላልተገባ እስር መዳረጋቸውን” የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል አስታወቀ። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ እንዳሉበት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል።  

አቶ ያሬድ ይህን ያሉት “በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ ያሉ ወቅታዊ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ አማራጮችን” በተመለከተ፤ ዛሬ እሁድ ታህሳስ 30፤ 2016 በተካሄደ የመድረክ ውይይት ላይ ነው። በአዲስ አበባው ካፒታል ሆቴል የተካሄደው ይህ የመድረክ ውይይት፤ በዛሬው ዕለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ የዋለውን የዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶች ቀን ለማክበር የተዘጋጀ ነበር።

በመድረክ ውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጹሁፍ ካቀረቡ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት አቶ ያሬድ፤ የሚመሩት ድርጅት ላለፉት ሶስት ዓመታት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የተፈጸሙ እስሮችን ዝርዝር መረጃ ማጠናቀሩን ተናግረዋል። “በ2023 ብቻ የተለቀቁትን ጨምሮ 50 የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ታስረዋል” ያሉት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር፤ “በቅርብ ጊዜ ራሱ ወደ ስድስት የሚጠጉ ጋዜጠኞች ከእስር እና ከመጉላላት በኋላ፤ እንደገና በስልክም በምንም በሚደርስባቸው ዛቻ እና ማስፈራሪያ ምክንያት ሀገር ጥለው ተሰድደዋል” ሲሉ አክለዋል።  

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) የተሰኘው አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አማካኝነት በተዘጋጀው በዛሬው ክብረ በዓል ላይ “አዲስ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ትውልድ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው 191 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የምረቃ ስነ ስርዓትም ተካሄዷል። ተመራቂዎቹ ተማሪዎች መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጽንሰ ሃሳብ ስልጠና የተከታተሉ ናቸው። ካርድ ለሶስት ዓመታት ባካሄደው ተመሳሳይ ስልጠና በአጠቃላይ 900 ተማሪዎችን ማስመረቁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)