የአውሮፓ ህብረት 27 አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ ዛሬ በቤልጄየም ብራስልስ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ይመክራሉ። ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር የተገናኙት የፈረንሳይ እና የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት ስብሰባ፤ የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ አማራጮች የሚመለከትበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ከሶስት ወራት በፊት በፕሪቶሪያ የተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት እና የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረው ቀጣይ ግንኙነት፤ የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት የዛሬ ስብሰባ የሚመክርባቸው ጉዳዮች እንደሚሆኑ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከምንጮች ተረድታለች። የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚመለከተው “ወቅታዊ ጉዳዮችን” በሚመለከትበት የስብሰባው ክፍል ነው።
በዚህ የስብሰባው ክፍል እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የኢራን፣ አርሜኒያ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዙዌላ እና ሞንቴኔግሮን ወቅታዊ ሁኔታዎች የተመለከቱ ሪፖርቶች ይቀርባሉ ተብሏል። ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የነበሩት፤ የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና እና የጀርመኗ አቻቸው አናሌና ቤርቦክ ለአውሮፓ አቻዎቻቸው ስለጉብኝታቸው ሪፖርት እንደሚያቀርቡም ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የጀርመኗ አቻቸው ኢትዮጵያን የጎበኙት፤ የትግራይ ተዋጊዎች ከባድ የጦር መሳሪያዎቻቸውን ለመከላከያ ሰራዊት ማስረከብ በጀመሩ ማግስት ነበር። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በአዲስ አበባ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ከነበረው ጦርነት በኋላ “በጎ መሻሻል” መኖሩን አስታውቀው ነበር።
የግጭት ማቆም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የታየው መሻሻል እንዲቀጥል እንደሚያበረታቱ የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና በዚሁ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ “ግጭት ቆሟል። እርዳታ ላልደረሳቸው ክልሎች መድረስ ጀምሯል። ትጥቅ መልሶ ማስረከብ ተጀምሯል” ሲሉም ታይተዋል ያሏቸውን መሻሻሎች ጠቅሰዋል።
ሁለቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 አንዴ እየጋመ ሌላ ጊዜ እየረገበ በተካሄደው ጦርነት፤ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ማቅረብ እንደሚያስፈልግም በወቅቱ ገልጸው ነበር። የኮሎና እና የቤርቦክ ምስክርነትም ሆነ ማሳሰቢያ፤ በጦርነቱ የሻከረውን የአውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚጠቁም ነው።
ለኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረውን ዓመታዊ የበጀት ድጋፍ በጦርነቱ ምክንያት ያቋረጠው የአውሮፓ ህብረት፤ የኢኮኖሚ ድጋፉን በሂደት ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ የፕሪቶሪያውን “በቋሚነት ግጭት የማቆም ስምምነት” ትግበራ በቅደመ ሁኔታነት ማስቀመጡ ይታወሳል። የአውሮፓ ህብረት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል የሚመሩት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት በዛሬው ስብሰባው የሚይዘው አቋም፤ የተቋረጠው የኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲቀጥል ሊያግዝ ይችላል የሚል ግምት አሳድሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)