ፍላጎታቸውን “በነፍጥ ማስፈጸም” በሚፈልጉ ኃይሎች ላይ፤ ህግ የማስከበር እርምጃ “ተጠናክሮ” እንደሚቀጥል ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ 

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ “በነፍጥ ፍላጎታቸውን የማስፈጸም ዓላማ አላቸው” ያላቸው አካላት ላይ፣ “ህግን የማስከበር ስራ” “በተጠናከረ መንገድ እንዲካሄድ” ውሳኔ ማስተላለፉን አስታወቀ። በሀገሪቱ የተሟላ ሰላም ለማስፈን፤ ከታጣቂ ቡድኖች ጋር የተጀመሩ “ሰላማዊ አማራጮች” ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መወሰኑንም ገልጿል።

ብልጽግና ፓርቲ ይህን ያስታወቀው ካለፈው ሰኞ ጥር 13፤ 2016 ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ያካሄዳቸውን የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎችን ሲያጠናቀቅ ባወጣው መግለጫ ነው። በሁለቱ ሰብሰባዎች ላይ “አበይት ሀገራዊ ጉዳዮች እና ልዩ ልዩ የፓርቲ አጀንዳዎች” ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።  

ፓርቲው በስብሰባዎቹ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል በኢትዮጵያ ያለውን የሰላም እና የጸጥታ ሁኔታ የሚመለከተው ይገኝበታል። “በጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት” የተፈጠሩ “ትስስሮች” አስከትለዋቸዋል የተባሉ ግጭቶች፤ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት “አንዱ እንቅፋት” መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል። 

እነዚህን ግጭቶች ለመፍታት፤ “ከታጣቂ ቡድኖች ጋር የተጀመሩ ሰላማዊ አማራጮች” ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ መቀመጡን ፓርቲው ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ለሁለት ጊዜ “የሰላም ንግግር” ማድረጉ ይታወሳል። ይህ የሰላም ንግግር ለሶስተኛ ጊዜ ሊቀጥል እንደሚችል፤ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።

ገዢው ፓርቲ “በሰላማዊ የፖለቲካ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን የሚያቀርቡ” ካላቸው አካላት ጋር “የሰላማዊ መንገዶች እንዲመቻቹ” ውሳኔ ማሳለፉን ቢያስታውቅም፤ ፍላጎታቸውን “በነፍጥ ማስፈጸም” በሚፈልጉ ኃይሎች ላይ ግን “የህግ ማስከበር” እርምጃን “በተጠናከረ መንገድ” መውሰዱን እንደሚቀጥል ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)