የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት “ዲሞግራፊ ለመቀየር” የሚካሄድ አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተባበሉ

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የመንገድ እና አካባቢ ልማት ፕሮጀክት፤ “ዲሞግራፊ ለመቀየር” አሊያም “ኦሮሞዎችን ወደ ከተማ ለመመለስ ነው” የሚሉ ወገኖችን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተቹ። አዲስ አበባ ውስጥ “ከበቂ በላይ” የኦሮሞ እና የሌሎች ብሔር ተወላጆች መኖራቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የሌለ ሰው ኖሮ፤ ሰው ለማምጣት የምንቸገርበት አይደለም” ሲሉም አስተባብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራን ከሚያስፈጽሙ አመራሮች እና የስራ ኃላፊዎች ጋር ትላንት ረቡዕ መጋቢት 18፤ 2016 ባደረጉት ውይይት ነው። እርሳቸው የሚመሩት መንግስት ከዚህ ቀደም ባከናወናቸው የግንባታ ስራዎች “ብዙ ስሞታዎች ነበሩ” ያሉት አብይ፤ ለዚህም የምኒልክ ቤተ መንግስት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እድሳትን በምሳሌነት አንስተዋል። 

“ይሄ ግቢ ሲቀየር ሀገራዊ ፖለቲካ ነበር። የእዚህን ግቢ እድሳትን እና ዩኒቲ ፓርክን ለመቃወም ሰዎች በጣም ብዙ ደክመዋል። በኋላ [የአዲስ አበባ ከተማ] ማዘጋጃ ቤት ሲጠናቀቅ፤ ‘ለምን ተሰራ’ ተብሎ ብዙ ተብሏል። አሁንም ብዙ አሉባልታዎች፤ ብዙ ወሬዎች ይሰማሉ። ‘ዲሞግራፊ ለመቀየር ነው’፤ ‘ኦሮሞዎች ለመመለስ ነው’ [የሚሉ] የተለያዩ ስሞች ይሰጣሉ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አብይ መንግስታቸው የአዲስ አበባ ከተማን “ዲሞግራፊ” የመቀየር እቅድ እንደሌለው ያስረዱት፤ የትውልድ ስፍራቸው የሆነችውን የበሻሻ ከተማ በምሳሌነት በመጥቀስ ነው። “ ‘ዲሞግራፊ መቀየር’ የሚባል ነገር የሚመጣው፤ በሻሻ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቋሚ ሰዎች የነበሩ ሆነው፤ ሰዎች ከጅማ፣ ከአጋሮ ከመጡ፤ በሻሻ እንዲገቡ እና እንዲቀላቀሉ ሲፈለግ የሚሰራ ስራ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ከአዲስ አበባ ከተማ ሁኔታ ጋር አነጻጽረዋል። 

“አዲስ አበባ ውስጥ፤ ከበቂ በላይ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ፣ ከበቂ በላይ ሁሉም አለበት። የሁለት፣ ሶስት ሚሊዮን ከተማ እኮ አምስት፣ ስድስት [ሚሊዮን] ገባ። የሌለ ሰው ኖሮ፤ ሰው ለማምጣት የምንቸገርበት አይደለም። አዲስ አበባስ የማን ከተማ ሆና ነው፤ ማን ዲሞግራፊ የሚሰቃይባት? አይገባኝም” ሲሉም ተደምጠዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የአዲስ አበባ የመንገድ ኮሪደር ልማት ዓላማ ከተማይቱ “ የሁሉም እና ውብ” እንድትሆን ማድረግ መሆኑን የጠቀሱት አብይ፤ ከ“ዲሞግራፊ መቀየር” ጋር ተያይዞ የሚሰሙ አስተያየቶችን “ወሬ እና አሉባልታ” ሲሉ አጣጥለዋቸዋል። “ይሄ ወሬ እና አሉባልታ የሚፈርሰው፤ በተግባር ሰርተን ስናሳይ ነው። ከተግባር ውጭ ይህንን ወሬ ሊያፈርስ የሚችል የለም” ያሉት አብይ፤ ፕሮጀክቱ “ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ” የሚተገበር ከሆነ “ሰው ለመገንዘብ አይቸገርም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባን “አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን እና ዘመናዊነት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰት ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሳድግ የሚችል” የተባለለት “የመንገድ ኮሪደር ልማት”፤ በከተማዋ ካቢኔ የጸደቀው ከአንድ ወር በፊት የካቲት 15፤ 2016 ነበር። በዚህ ፕሮጀክት እንዲለሙ ዕቅድ የተያዘላቸው የመንገድ ኮሪደሮች፤ ዓለም አቀፍ “የስማርት ሲቲ” ስታንዳርድን በማሟላት የአዲስ አበባ ከተማን ደረጃ “ከፍ የሚያደርጉ ናቸው” ሲል የከተማይቱ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)