በኤርትራ ታስረው የነበሩ 46 የትግራይ ክልል ተወላጆች ተለቀቁ 

በሰለሞን በርሀ

ለሁለት ዓመታት በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ወቅት፤ ወደ ኤርትራ ተወስደው ታስረው ከነበሩ የክልሉ ተወላጆች ውስጥ አርባ ስድስቱ በዛሬው ዕለት ተለቀቁ። እስረኞቹ ዛሬ አርብ ሚያዝያ 4፤ 2016 ጠዋት ሽራሮ ከተማ መግባታቸውን የከተማይቱ ከንቲባ አቶ ሙሉ ብርሃነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

እስረኞቹ በጦርነቱ ጊዜያት ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በኤርትራ ሰራዊት ተይዘው ከተወሰዱ በኋላ፤ በኤርትራ የጋሽ ባርካ ዞን መቀመጫ በሆነችው የባረንቱ ከተማ ታስረው የቆዩ መሆናቸውን አቶ ሙሉ ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው የተፈቺዎች ዝርዝር፤ የአብዛኞቹ መኖሪያ አድራሻ በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን ውስጥ ባሉ አካባቢዎች የሚገኝ ነው። 

ከኤርትራ ጋር በሚዋሰነው በዚህ ዞን ስር ከሚገኙ አካባቢዎች ውስጥ በርካታ ነዋሪዎቿ የተወሰዱባት የሽራሮ ከተማ ትገኝበታለች። እስረኞቹ ዛሬ ጠዋት በ”አይሱዙ” ተሽከርካሪ ተጭነው ሽራሮ ሲደርሱ፤ የከተማይቱን ከንቲባ ጨምሮ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሰሜን ምዕራብ ዞን አስተዳደር አመራሮች እና የጸጥታ አካላት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በእስር ላይ የቆዩት የትግራይ ተወላጆች “ምህረት ተደርጎላቸው” የተለቀቁት፤ በኢፌዲሪ የመከላከያ ሰራዊት እና በኤርትራ ሰራዊት መካከል ሲካሄድ በቆየ ንግግር መሆኑን አቶ ሙሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። አርባ ስድስቱ እስረኞች ተለቅቀው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገው፤ በጦርነቱ ጊዜ “ከባድ ወንጀል ያልፈጸሙ ናቸው” በሚል ምክንያት መሆኑ ተነግሯል። 

በኤርትራ በእስር ላይ ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች መካከል አሁንም ያልተፈቱ ቢኖሩም፤ የዛሬው እርምጃ የቀሩትም እንደሚለቀቁ “ተስፋ ሰጪ ነው” ሲሉ የሽራሮ ከተማ ከንቲባ በበጎ መልኩ ተቀብለውታል። ለዚህም በማስረጃነት የሚጠቅሱት፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከመመስረቱ በፊት በተመሳሳይ መልኩ የተለቀቁ 400 ገደማ የትግራይ ተወላጆች መኖራቸውን ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)