በኢትዮጵያ በጎርፍ ሳቢያ የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት ምን ያህል ነው?  

በኢትዮጵያ ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ከ590 ሺህ በላይ ሰዎች መጠቃታቸው እና 95 ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት ተቋማት ባለፉት ቀናት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። በጎርፍ የተጠቁት አካባቢዎች የሚገኙት በዘጠኝ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሆናቸውንም የተቋማቱ ሪፖርት አመልክቷል። 

ከክልሎች መካከል በጎርፍ ብርቱ ጉዳት ያስተናገደው የሶማሌ ክልል መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) አስታውቋል። በክልሉ በአፍዴር፣ ሊበን እና ሸበሌ ዞኖች የሚገኙ አካባቢዎች በጎርፍ በመጥለቅለቃቸው ከ247 ሺህ ሰዎች በላይ መጠቃታቸውን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። በእነዚህ ዞኖች ቢያንስ 51 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንም ጽህፈት ቤቱ ይፋ አድርጓል። 

በሶማሌ ክልል የሚገኙት የሸበሌ፣ ገናሌ እና ዌብ ወንዞች ከግንቦት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ መቀነስ ቢያሳዩም፤ በአካባቢው ሊጥል በሚችለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ወንዞቹ ሊሞሉ ስለሚችሉ አሁንም ክትትል እንደሚያስፈልግ የመንግስታቱ ድርጅት ጽህፈት ቤት በሪፖርቱ አሳስቧል። በሶማሌ ክልል ባለፈው ጥቅምት እና ህዳር ወር በነበረው የዝናብ ወቅት፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በጎርፍ ተጠቅተው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ የነበረው ጎርፍ በመሰረተ ልማቶች ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በርካታ ከብቶችንም ለሞት ዳርጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)