በነዳጅ ግብይት ተዋናዮች ላይ እስከ ሰባት ዓመት እስራት የሚያስከትሉ ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው?

ህገ ወጥ ድርጊት ፈጽመው በተገኙ “የነዳጅ ግብይት ተዋናዮች” ላይ የሚጣል የእስራት እና የገንዘብ ቅጣትን የያዘ የህግ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። በአዋጅ ረቂቁ የተዘረዘሩ ህገ ወጥ ድርጊቶች፤ ከሶስት እስከ ሰባት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲሁም የነዳጅ ውጤቶችን መወረስ የሚያስከትሉ ናቸው።

“የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ስርዓት ለመደንገግ” የተዘጋጀው ይህ የአዋጅ ረቂቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው፤ ትላንት ማክሰኞ ሰኔ 4፤ 2016 በተካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። በአዋጅ ረቂቁ የቅጣት ድንጋጌ ማካተት ያስፈለገው፤ “በዘርፉ ከሚፈጸመው የሕግ ጥሰት አይነት እና ክብደት ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ቅጣቶች በወንጀል ሕጉ ባለመካተቱ” መሆኑ ተገልጿል። 

በአዲሱ የህግ ረቂቅ እስከ ሰባት ዓመት ጽኑ እስራት የሚያስከትሉ ድርጊቶች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል፤ “የነዳጅ ውጤቶችን ወደ ጎረቤት ሀገር በኮንትሮባንድ ማጓጓዝ” የሚለው ይገኝበታል። “የተረከባቸውን የነዳጅ ውጤቶች ከተፈቀደለት የማጓጓዣ መስመር ውጪ ሲያጓጉዝ የተያዘ” እና “ከተፈቀደለት ማራገፊያ ውጪ ሲያራግፍ” የተገኘ ግለሰብም በተመሳሳይ ከሶስት እስከ ሰባት ዓመት እስራት ይጠብቀዋል። 

በእነዚህ ህገ ወጥ ድርጊቶች የተሳተፈ ግለሰብ ሲያጓጉዛቸው የነበሩ የነዳጅ ውጤቶች እንደሚወረሱም የአዋጅ ረቂቁ ይደነግጋል። “የነዳጅ ውጤቶችን ሆን ብሎ ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ማቅረብም”፤ ሌላው ከሶስት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑ በአዋጅ ረቂቁ ተመልክቷል። 

አዲሱ አዋጅ “የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፤ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ ቦታ እና የግብይት ስርአት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ ወይም በመመሪያ በተወሰነው መሠረት አደጋ ያስከትላሉ በተባሉ መያዣዎች ሲሸጥ የተገኘ ሰው” ከ3 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚቀጣ አስፍሯል። ይህም ድርጊት የነዳጅ ውጤቶችን መወረስ ያስከትላል። 

“አግባብ ካለው አካል በጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኝ፤ የነዳጅ ውጤቶችን የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ሲሸጥ የተገኘ” ሰውም እንዲሁ የተያዘበት የነዳጅ ውጤት ይወረስበታል። ይህን ድርጊት ፈጽሞ የተገኘ ሰው፤ ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት እና ከ25 ሺህ ብር እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ በአዋጁ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)