“ማናቸውም አይነት ተጽእኖ ደርሶብን አያውቅም፤ ቢደርስብንም አንቀበልም” – ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

በተስፋለም ወልደየስ

የሰብአዊ መብት ተቋማት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወይም አጋር ሀገራት ገንዘብ ማሰባሰባቸው፤ “ነጻነታቸውን የሚቃረን” ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ተናገሩ። እርሳቸው የሚመሩት ተቋም ከአለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ገንዘብ ቢያሰባስብም፤ “ማናቸውም አይነት ተጽእኖ” ደርሶበት እንደማያውቅም ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ይህን ያሉት፤ የሰብአዊ መብት ተቋማትን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በትላንትናው ዕለት ለሰነዘሩት ትችት በሰጡት ምላሽ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ትላንት ሐሙስ ሰኔ 27፤ 2016 በተካሄደ የፓርላማ ስብሰባ ላይ የሰብአዊ መብት ተቋማትን እና አሰራራቸውን “መፈተሽ” እንደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር። 

አብይ በዚሁ ንግግራቸው የሰብአዊ መብት ተቋማት ከሌሎች ሀገራት እና ፍላጎቶች ተጽእኖ “ነጻ መሆን” እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እኛ ደመወዝ የማንከፍለው፣ ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን፤ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናንተ መተው ነው” ሲሉም የመገመቱን ድርሻ ለፓርላማ አባላት ትተው ነበር።

ዛሬ አርብ ሰኔ 28፤ 2016 በኢሰመኮ ዋና መስሪያ ቤት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ በሰብአዊ መብት ተቋማት ላይ ያነጣጠረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትችት በጋዜጠኞች ተነስቶ ነበር። ይህን መሰሉ ትችት “በመንግስት በጀት የማይተዳደሩ” የሰብአዊ መብት ተቋማት ላይ “ብዙ ጊዜ ይቀርባል” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ ጉዳዩ በሌሎች ሀገራትምም “የተለመደ እና በተደጋጋሚ የሚሰማ” እንደሆነ አመልክተዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ኢሰመኮም ከአለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች “ሀብት የሚያሰባስብ” መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ዳንኤል፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ ለተቋማቸው በመንግስት የሚመደበው በጀት ስራዎችን ለማከናወን “በቂ ስላልሆነ” እንደሆነ አስረድተዋል። ትላንት በፓርላማ በጸደቀው የ2017 የፌደራል መንግስት በጀት ውስጥ፤ ለኢሰመኮ የተመደበው መደበኛ በጀት 130.4 ሚሊዮን ብር ነው።

የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተቋም በመንግስት ከሚመደብለት በተጨማሪ ከእርዳታ፤ ከስጦታ እና ከማናቸውም ሌላ ምንጭ በጀት ማግኘት እንደሚችል ይደነግጋል። እንደ ኢሰመኮ ሁሉ ሌሎችም የሰብአዊ መብት ተቋማት “ሃብት ማሰባሰባቸው በራሱ ስህተት አይደለም” ሲሉ ዶ/ር ዳንኤል በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።     

“የተወሰኑ መንግስታዊ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ መንግስትም፣ ከአለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ሀብት ያሰባስባል። ስለዚህ ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ወይም አጋር ሀገራት፤ ሀብት እና ገንዘብ ማሰባሰብ በራሱ የተቋምን ነጻነት የሚቃረን ነገር አይደለም” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ አክለዋል። ዶ/ር ዳንኤል የሚመሩትን ተቋም በምሳሌነት በማንሳት፤ “ተጽእኖን” በተመለከተ ስለሚቀርበው ትችትም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“መንግስትም በጀት ይመድብልናል። ከአጋር ድርጅቶችም ለስራችን የሚያስፈልገንን የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ እናስተባብራለን። ይሄ ማለት ግን ከየትኛውም ወገን፣ ከመንግስትም ይሁን ከመንግስት ውጪ በስራችን ላይ አንዳችም አይነት፣ ማናቸውም አይነት ተጽእኖ ደርሶብን አያውቅም። ቢደርስብንም አንቀበልም። ያለ ተጽእኖ የምንሰራ ተቋም ነን” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም አስታውቀዋል። 

“[ኢሰመኮ] ለኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለኢትዮጵያ ህዝብ ተጠሪ የሆነ፤ ጠንካራ፣ ነጻ፣ ገለልተኛ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋም ነው” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ ተቋሙ ስራዎቹን የሚያከናውነው በሰብአዊ መብቶች “መርሆዎች እና ስምምነቶች” እንዲሁም “በኢትዮጵያ ህግ እና ደንብ” መሰረት መሆኑን አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)