በሙሉጌታ በላይ
በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ከተከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ በቀዳሚነት አሳሳቢ የሆነው፤ በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰው የሞት እና የአካል ጉዳት መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ። በርካታ ሰዎች ለሞት እና ለአካል ጉዳት የተዳረጉት፤ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖች በተወሰዱ እርምጃዎች መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ብሔራዊው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ይህን የገለጸው፤ “የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ” የዳሰሰ ዓመታዊ ሪፖርት ዛሬ ሰኔ 28፤ 2016 በዋና መስሪያ ቤቱ ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው። ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ 2016 ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍነው ይህ ሪፖርት፤ አሳሳቢ እና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን፣ መልካም እምርታዎችን እና ምክረ ሀሳቦችን የያዘ ነው።
በሶስት ክፍሎች የተሰናዳው ባለ 132 ገጽ ዓመታዊ ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ “ጠቅለል ባለ መልኩ የሚያሳይ” መሆኑን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል። ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ውስጥ “የተከሰቱ የሁሉም ክስተቶች እና የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ሙሉ ስብስብ” አለመሆኑን አስገንዝበዋል።
በመጪው ሐምሌ ወር መጨረሻ ከኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ኃላፊነታቸው የሚሰናበቱት ዶ/ር ዳንኤል፤ ባለፈው አንድ አመት “አሳሳቢ ሆነው ቀጥለዋል” ባሏቸው የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል። “በሪፖርት ዘመኑ አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው በህይወት የመኖር መብት ነው” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች “የትጥቅ ትግል ሁነቶች” መኖራቸው ሲቪል ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት መሆኑንም ዶ/ር ዳንኤል በዛሬው መግለጫ ላይ አንስተዋል። “ሲቪል ሰዎችን በጥንቃቄ ባለዩ የተፋላሚ ወገኖች ውጊያዎች እንዲሁም ሲቪል ሰዎች ላይ ባነጣጠሩ እና በታጠቁ ቡድኖች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል” ብለዋል የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር።
“በትጥቅ ግጭት አውድ ውስጥ ሆነ ከትጥቅ ግጭት አውድ ውጭ የሚፈጸሙ ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች እና አስገድዶ ገንዘብ መቀበል ወይም ታጋቾችን መግደል፤በታጠቁ ቡድኖች የሚፈጸሙ የሰዎች እገታ እና አስገድዶ ገንዘብ መቀበል ወይም ታጋቾችን መግደል በተመሳሳይ አሳሳቢ ሆኖ የቀጠለ ችግር ነው። በግጭት አውዱ እና በታጠቁ ቡድኖች ጥቃት የተነሳ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አደጋ ላይ እንደወቀ ቀጥሏል” ሲሉ ዶ/ር ዳንኤል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ካሉ 12 ክልሎች ውስጥ ገሚሱ “የትጥቅ ትግል ሁነቶች” እንደሚካሄድባቸው በኢሰመኮ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል። በተለይ በትጥቅ ግጭት ውስጥ በቆዩት የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች፤ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች “መቀጠላቸውን እና እየተስፋፉ መምጣታቸውን” ኢሰመኮ በሪፖርቱ አመልክቷል።
በአማራ ክልል ለአስር ወራት ተደንግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ አጠቃላይ የሰብአዊ ሁኔታ ላይ “ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ” ያሳደረ እንደነበር ዶ/ር ዳንኤል ተናግረዋል። ከአማራ ክልል በተጨማሪ እንዳስፈላጊነቱ “በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ” ተፈጻሚነት የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው በሐምሌ 2015 ዓ.ም. ነበር።
ኢሰመኮ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ከተሰጡት ስልጣኖች እና ኃላፊነቶች መካከል፤ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሰብአዊ መብቶችን መከታተል” የሚለው አንዱ ነው። እስካለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ በቆየው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “በርካታ ሰዎች ያለ ኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ መደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ውስጥ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸውን” ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቆይታ ወቅት “ለቀናት እና ሳምንታት ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ” ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንደነበሩም ኮሚሽኑ ገልጿል። በዚሁ ጊዜ የታሰሩ ጋዜጠኞች ብዛት 11 እንደነበር በኢሰመኮ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጸንቶ በቆየባቸው ጊዜያት ውስጥ፤ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የማህብረሰብ አንቂዎች እና በህዝባዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሰዎች “ከኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ ውጪ ለእስራት ተዳርገዋል” ሲል ሪፖርቱ አትቷል።
“ከህጋዊ ስርዓት ውጭ የሚፈጸም የዘፈቀደ እስር” እና “የአስገድዶ መሰወር” በብዙ አካባቢዎች አሁንም አሳሳቢነቱ መቀጠሉን ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ማጣራቱም በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር “አሁንም [ድረስ] ያሉበት ቦታ የማይታወቁ ሰዎች እና ከህጋዊ ስርዓት ውጭ በእስር የሚገኙ ሰዎች አሉ” ሲሉ ጉዳዩ አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)