በድጋሚ እና ቀሪ ምርጫ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁለት የፓርላማ መቀመጫ አሸነፉ 

ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዲስ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ውጤት ይፋ ተደርጓል     

በሙሉጌታ በላይ

በሰኔ ወር አጋማሽ በአራት ክልሎች በተካሄደው “ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ”፤ ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁለት የፓርላማ መቀመጫ አሸነፉ። በባለፈው ጠቅላላ ምርጫ ያልተደረገባቸውን አብዛኞቹን የክልል ምክር ቤት እና የፓርላማ መቀመጫዎች፤ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል።

በአፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰኔ 16፤ 2016 በተካሄደው “ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ”፤ 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና 12 የግል ዕጩዎች እንደተሳተፉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በዚሁ ምርጫ ዘጠኝ የፓርላማ እና የ108 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ለውድድር ቀርበዋል።

ሶስት የፓርላማ መቀመጫዎች ለምርጫ በቀረቡበት በአፋር እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች፤ ሁሉንም ያሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ መሆኑን ምርጫ ቦርድ ትላንት ቅዳሜ ሰኔ 29፤ 2016 ይፋ ያደረገው ውጤት አመልክቷል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውድድር ከተደረገባቸው ስድስት የፓርላማ መቀመጫዎች፤ አራቱን ያሸነፈው ገዢው ፓርቲ መሆኑንም ቦርዱ አስታውቋል። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁለት ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች በለስ ቀንቷቸዋል። የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) አንድ የፓርላማ ወንበር ሲያሸንፍ፤ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) በተመሳሳይ አንድ መቀመጫ ማሸነፍ ችሏል። ሁለቱ ፓርቲዎች፤ በክልል ምክር ቤትም የተወሰኑ መቀመጫዎችን አሸንፈዋል። 

በሰኔ 16ቱ ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውድድር የተደረገባቸው የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት 71 ነበር። ጉህዴን ከእነዚህ መቀመጫዎች ውስጥ ስምንቱን ሲያሸንፍ፤ ቦዴፓ በበኩሉ ሶስት ተወካዮቹን ለክልሉ ምክር ቤት ማስመረጥ ችሏል። ቀሪዎቹ 60 መቀመጫዎችን አሸንፎ ምርጫውን በበላይነት ያጠናቀቀው ብልጽግና ፓርቲ ነው። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ካሉት 99 መቀመጫዎች ውስጥ በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ድምጽ መስጠት የተካሄደባቸው በ28ቱ ብቻ መሆኑ ይታወሳል። “በጸጥታ ችግር ምክንያት” በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ምርጫ ሳይካሄድ በመቅረቱ፤ በክልሉ አዲስ መንግስት ለመመስረት የሚያስፈልገው የመቀመጫ መጠን ሳይሟላ ቀርቷል።

አሁን ክልሉን እያስተዳደሩ ያሉት አመራሮች የተሾሙት፤ ከዘጠኝ ዓመት በፊት በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በተመረጡ የክልል ምክር ቤት አባላት አማካኝነት ነው። በአሁኑ ምርጫ፤ ለቀሪዎቹ የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ተወካዮች መመረጣቸው ይፋ በመደረጉ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሶስት ዓመት ዘግይቶም ቢሆን አዲስ መንግስት ለመመስረት ይችላል።

እንደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁሉ፤ ገዢው ፓርቲ ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች በተወዳደረባቸው ሌሎች ሶስት ክልሎች ማሸነፉን ምርጫ ቦርድ በትላንቱ መግለጫው አስታውቋል። በአፋር ክልል 27፣ በሶማሌ ክልል 7፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 3 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን፤ ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም መቀመጫዎች ማሸነፉን ቦርዱ ገልጿል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስቀድሞ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ፤ የምርጫ ውጤት ይፋ የሚሆነው ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 27፤ 2016 ዓ.ም ነበር። ይፋዊ ውጤቱ ሁለት ቀናት የዘገየው፤ ብልጽግና ፓርቲ ከ150 ምርጫ ጣቢያዎች በላይ  አቤቱታዎች በማቅረቡ እንደሆነ የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ በትላንቱ መርሃ ግብር ላይ ተናግረዋል።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የምርጫ ሂደቱን አስመልክቶ ገዢው ፓርቲ ላቀረባቸው ለእነዚህ አቤቱታዎች፤ “ውጤት ይፋ ከመሆኑ በፊት ውሳኔ ለመስጠት ሲባል”፤ ቀኑ እንዲራዘም መደረጉንም ምክትል ሰብሳቢው አብራርተዋል። ከብልጽግና ፓርቲ በተጨማሪ ሌሎች  ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አራት የግል እጩዎች ቅሬታ ማቅረባቸውን ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሰኞ በሰጠው መግለጫ አስታውቆ ነበር።

ቅሬታቸውን ያቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የቤንሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን)፣ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) እና የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ናቸው። በተመሳሳይ መልኩ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የግል ዕጩዎች የተወዳደሩት፤ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ነው። 

በሶማሌ ክልል ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሶስት ዕጩዎች ሁሉም  ጅግጅጋ ቁጥር ሁለት በተሰኘ የምርጫ ክልል ላይ የተወዳደሩ መሆናቸውን በምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስራ ኃላፊ ቀነኒ እንሰርሙ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባለፈው ሰኞ ተናግረው ነበር። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኘው መስቃን እና ማረቆ የምርጫ ክልል የተወዳደሩ አንድ የግል እጩም እንዲሁ ቅሬታ ማቅረባቸውን ኃላፊዋ አስረድተዋል።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

በስምንት የምርጫ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ “የተለያዩ ጥሰቶች ተፈጽመዋል” የሚል ቅሬታ ያቀረቡት ፓርቲዎች እና የግል እጩዎች፤ “ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ” እንዳለባቸው ኃላፊዋ አመልክተዋል። ቦርዱ የቀረቡለትን ቅሬታዎች “በተለያየ ደረጃ የማጣራት ስራ እየሰራ” መሆኑንም ባለፈው ሰኞ አስታውቀው ነበር። 

የ“ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ” አስመልክቶ ለቦርዱ ከቀረቡ ቅሬታዎች ውስጥ፤ ምርመራቸው የተጠናቀቀው “በቦርዱ ውሳኔ” እንደተሰጠባቸው ተነግሯል። ይፋዊ የምርጫ ውጤቱ ከመገለጹ አስቀድሞም፤ ቅሬታውን ላቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎች በደብዳቤ እንደተገለጸላቸውም ቦርዱ አስታውቋል። 

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ፤ “በምርጫ ሂደት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች አስተዳደራዊ መፍትሄ” የመስጠት ኃላፊነት በማቋቋሚያ አዋጁ ተሰጥቶታል። ቦርዱ በምርጫ ሂደት “የምርጫ ውጤትን የሚያዛንፍ የህግ ጥሰት ተፈጽሟል” ብሎ ሲያምን፤ “ውጤቱን የመሰረዝ” እና “ድጋሚ ምርጫ የማካሄድ” ስልጣንም በአዋጁ ተሰጥቶታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)