ዓመታዊ “የስራ ክንውን ሪፖርት አላቀረቡም” የተባሉ 205 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈረሱ

በናሆም አየለ

ለሶስት ተከታታይ ዓመት የስራ ክንውን እና የኦዲት ሪፖርት ያላቀረቡ 205 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መፍረሳቸውን እነርሱን የመከታተል እና የመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው ባለስልጣን መስሪያ ቤት አስታወቀ። ከፈረሱት ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር፣ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሃኪሞች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያዎች ማህበር እና ሚዩዜክ ሜይ ዴይ ኢትዮጵያ ይገኙበታል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራቸውን በህግ አግባብ ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ፤ አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር የማድረግ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ነው። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ዓመታዊ የስራ እና የገንዘብ እንቅስቃሴ ሪፖርት የመመርመር ስልጣንም በ2011 ዓ.ም. በተሻሻለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ተሰጥቶታል። 

በዚሁ አዋጅ መሰረት፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የእያንዳንዱን በጀት ዓመት ዋና ዋና ክንዋኔዎችን የሚያሳይ ሪፖርት “የበጀት ዓመቱ ባለቀ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ” ለባለስልጣኑ ማቅረብ አለባቸው። ድርጅቶቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሪፖርት ካላቀረቡ፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የድርጅቶቹን ህልውና ለማረጋገጥ በጋዜጣ ጥሪ እንደሚያደርግም በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። 

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህንኑ መሰረት በማድረግ፤ ከ2013 ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ዓመታት “የስራ ክንውን እና ኦዲት ሪፖርት አላቀረቡም” ላላቸው ድርጅቶች “ተደጋጋሚ ጥሪ” ማድረጉን በደብዳቤ አስታውቋል። ባለስልጣኑ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ሰኔ 24፤ 2016 በጻፈው ደብዳቤ፤ “ህልውናቸውን ማረጋገጥ አልቻሉም” በሚል የዘረዘራቸው ድርጅቶች ብዛት 205 ነው። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን “በጋዜጣ እና በተለያዩ ሚዲያዎች” በመጀመሪያ ጥሪ ያደረገላቸው ድርጅቶች ብዛት 293 እንደነበር በመስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ ትግስት ዳኝነት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በድርጅቶቹ መፍረስ ላይ የመወሰን ስልጣን ያለው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቦርድ ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ፤ ድርጅቶቹ እስከ ሰኔ 30፤ 2016 ህልውናቸውን እንዲያረጋግጡ ቀነ ገደብ አስቀምጦ እንደነበር አስታውሰዋል።

በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአካል ቀርበው ሪፖርት ያላቀረቡበትን ምክንያት ያስረዱት 88 ድርጅቶች የገለጹት ወ/ሮ ትግስት፤ እነዚህ ድርጅቶች እንዳይፈርሱ መደረጉን ገልጸዋል። በተቀሩት 205 ድርጅቶች ላይ ግን ቦርዱ የወሰነው የመፍረስ ውሳኔ መጽናቱን አስገንዝበዋል። 

“እስከ ሐምሌ አንድ ካልመጡ ‘ውሳኔው ይጽና’ ብሎ ነው ቦርዱ የወሰነው። የመጨረሻ ውሳኔ ነው”

ወ/ሮ ትግስት ዳኝነት፤ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ

“እስከ ሐምሌ አንድ ካልመጡ ‘ውሳኔው ይጽና’ ብሎ ነው ቦርዱ የወሰነው። የመጨረሻ ውሳኔ ነው” ሲሉ ወ/ሮ ትግስት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል። በቦርዱ ውሳኔ መሰረት ከትላንት ሰኞ ሐምሌ 1፤ 2016 ጀምሮ መፍረሳቸውን ይፋ ከተደረጉ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር ይገኝበታል።

የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሃኪሞች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያዎች ማህበር እና የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበርም እንደዚሁ በፈረሱ ድርጅቶች ዝርዝር ተካትተዋል። የቀድሞ ምድር ጦር ሰራዊት እና ሲቪል ሰራተኞች ማህበር እና ምሳሌ ራስ አገዝ የጦር ጉዳተኞች ማህበር የተባሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም እንዲሁ ህልውናቸው መክሰሙ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ደብዳቤ ላይ ሰፍሯል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ፊርማን የያዘው ይህ ደብዳቤ፤ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የተገናኙ ሁለት ድርጅቶች መፍረሳቸውንም አመልክቷል። የመጀመሪያው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፋውንዴሽን” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ንብረትነቱ የአየር መንገዱ በሆነው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ላይ በደረሰ የመከስከስ አደጋ ተጎጂ የሆኑ ቤተሰቦች ያቋቋሙት ማህበር ነው። 

የበረራ ቁጥሩ ET 302 የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን፤ በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ ጊምቢቾ ወረዳ የተከሰከሰው መጋቢት 1፤ 2011 ዓ.ም ነበር። ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ አየር ማረፊያ ሲበር በነበረው በዚህ አውሮፕላን የተሳፈሩ 149 መንገደኞችን እና ስምንት የበረራ ሰራተኞች በሙሉ በአደጋው መሞታቸው ይታወሳል። 

በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦች ካቋቋሙት ማህበር በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጡረተኞች ማህበር እና በአዲስ አበባ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተከራዮች ማህበርም በተመሳሳይ ሁኔታ መፍረሳቸው ተገልጿል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን መፍረሳቸውን ካሳወቃቸው ውስጥ ዘጠኙ “የውጭ ድርጅቶች” ናቸው።

በውጭ ሀገር ህግ መሰረት ተቋቋመው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመዝግበው ሲንቀሳቀሱ ከቆዩት ከእነዚህ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በኦባንግ ሜቶ የሚመራው ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ይገኝበታል። “ዩዝ ፎር ሴኩሪቲ አፍሪካ ኢትዮጵያ ኔትወርክ”፣ “ግሎባል ሪሌሽንስ” እና “ስቱድፋስት ቮለንተሪ ኦርጋናይዜሽን” የተባሉ የውጭ ድርጅቶችም መፍረሳቸው ተገልጿል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እንዲፈርሱ ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ድርጅቶች፤ ንብረታቸው ወዲያውኑ በመስሪያ ቤቱ በሚሾም  ሒሳብ አጣሪ ኃላፊነት ስር እንደሚሆን በአዋጅ ተደነግጓል።  ሒሳብ አጣሪው “ከድርጅቱ ዓላማ ጋር የተያያዙ እና ሊቋረጡ የማይችሉ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ካልሆነ በስተቀር” ሌላ ተግባር ማከናወን እንደማይችል በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

የድርጅቱን ዕዳዎች እና የማፍረስ ሂደቱን ለማከናወን የሚያስፈልጉ ወጪዎች ተጠናቅቀው ከተከፈሉ በኋላ፤ የድርጅቱ ቀሪ ገንዘብ እና ንብረት “ለሌላ ድርጅት እንዲተላለፍ እንደሚደረግ” በአዋጁ ተመልክቷል። የድርጅቱ የሒሳብ ማጣራት ስራዎች ሲጠናቀቁም፤ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሒሳብ አጣሪው ጠያቂነት “ድርጅቱን ከመዝገብ እንደሚሰርዝ” በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)