በሙሉጌታ በላይ
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ፤ ከሶማሊያ ጋር የገባችበትን ውዝግብ ለማሸማገል በሚደረገው ጥረት ላይ ለመወያየት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን ነገ ቅዳሜ ሐምሌ 27፤ 2016 ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው። ሐካን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀስላሴ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሌላንድ የባህር ወደብን ለማልማት የመግባቢያ ስምምነት የፈረሙት ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ነበር። ይህ የመግባቢያ ስምምነት፤ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ የራሷን የጦር ሰፈር እንድትገነባ መንገዱን የሚጠርግላት እንደሆነ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ይፋ ተደርጓል።
የሶማሊያ መንግስት “ያለ እኔ እውቅና፤ የግዛቴ አካል ከሆነችው ሶማሌላንድ ጋር ምንም አይነት ስምምነት ሊደረግ አይችልም” ሲል የመግባቢያ ስምምነቱን አጥብቆ ሲቃወም ቆይቷል። በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በንግግር ለመፍታት፤ ቱርክ ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ለማሸማገል ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
ቱርክ በነገው ዕለት አዲስ አበባ በሚገቡት ከፍተኛ ዲፕሎማቷ አማካኝነት፤ የሁለቱን ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ወደ አንካራ በመጋበዝ እንዲወያዩ አድርጋለች። የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፊት ለፊት ያልተገናኙበት ይህ ውይይት “መፍትሔ በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ” እንደነበር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
የአንካራው የመጀመሪያ ዙር ውይይት ያለ ውጤት ቢጠናቀቅም፤ ሁለቱ ሀገራት ዳግም ለመገናኘት ለነሐሴ 27፤ 2016 ቀጠሮ ይዘው መለየየታቸው ይታወሳል። ይህ ቀነ ቀጠሮ ከመድረሱ ከአንድ ወር በፊት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ከሶማሊያ ጋር ስለተጀመረው የሽምግልና ሂደት ይነገጋራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሀገሪቱ መንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ “ቲአርቲ ወርልድ” ዘግቧል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ከዚህ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር “በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች” ላይ እንደሚወያዩ ዘገባው ጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)