በቤርሳቤህ ገብረ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመንገድ ኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ በፒያሳ አካባቢ ላጸዳቸው ሶስት ቦታዎች፤ በካሬሜትር እስከ 268 ሺህ ብር ድረስ የመሬት ሊዝ ዋጋ ቀረበባቸው። የመሬት ሊዝ ዋጋዎቹ፤ ባለፈው ግንቦት ወር በዚሁ አካባቢ ለጨረታ ለቀረቡ ቦታዎች ከተሰጠው ያነሰ ነው።
በፒያሳ ሲኒማ አምፒር አካባቢ ለሚገኙት ሶስት ቦታዎች የቀረቡ የመጫረቻ ዋጋዎች በይፋ የተከፈቱት ትላንት ሰኞ ሐምሌ 29፤ 2016 በተካሄደ ስነ ስርዓት ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኙትን እነዚህን ቦታዎች ጨምሮ፤ በስምንት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 7.8 ሄክታር ስፋት ያላቸው መሬቶች ለጨረታ ያቀረበው በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።
ሆኖም ለእነዚህ ቦታዎች በቂ ተጫራች ባለመገኘቱ፤ የከተማይቱ መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ጨረታውን ለተጨማሪ 10 ቀናት ለማራዘም ተገድዷል። የመሬት ሊዝ ጨረታው በትላንትናው ዕለት በተከፈተበት ወቅት፤ በአጠቃላይ ከአራት ሺህ በላይ የጨረታ ሰነዶች መሸጣቸው ተገልጿል።
በዚሁ ስነ ስርአት ላይ በፒያሳ አካባቢ ለሚገኙ ሶስት ቦታዎች ከተወዳደሩ ተጫራቾች ውስጥ፤ ከፍተኛው መጠን ያቀረበው አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ መሆኑ ታውቋል። ባንኩ 1,157 ካሬ ሜትር ስፋት ላለው መሬት ያቀረበው ዋጋ በካሬ ሜትር 268 ሺህ ብር ነው። ተጫራቹ በጨረታ ማመልከቻው ላይ 51 በመቶ ቅድመ ክፍያ ለማስገባት መስማማቱንም አስታውቋል።
በፒያሳ አካባቢ ለጨረታ ከቀረቡት መሬቶች በመጠን አነስተኛ ለሆነው ለዚህ ቦታ፤ ሁለተኛውን ከፍተኛ ዋጋ ያቀረበው በርዬ ሪል ስቴት የተባለ ድርጅት ነው። የሪል ስቴት አልሚው ድርጅት ለቦታው በካሬ ሜትር 96,513 ብር ሲያቀርብ፤ በተመሳሳይ የስራ ዘርፍ የተሰማራው ሪሀ ሪል ስቴት አክሲዮን ማህበር በበኩሉ በካሬ ሜትር 66,666 ብር የመወዳደሪያ ዋጋ አስገብቷል።
በዚሁ አካባቢ ጨረታ ከወጣባቸው መሬቶች በመጠን ከፍተኛ የሆነው ቦታ 4,798 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ነው። ለዚህ ቦታ የላቀውን ዋጋ ያቀረበው ፊልተማ ትሬዲንግ የተባለ ድርጅት ነው። በካሬ ሜትር በ167 ሺህ ብር መጫረቻ ዋጋ ያቀረበው ድርጅቱ፤ ለከተማይቱ መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ 40 በመቶ ቅድመ ክፍያ ለመፈጸም መስማማቱን በጨረታ ማመልከቻው ላይ አስፍሯል።
በሲኒማ አምፒር አካባቢ ከሚገኙት ሁለቱ ቦታዎች አቅራቢያ የሚገኝ 1,235 ካሬ ሜትር ቦታም በተመሳሳይ ሁኔታ ለጨረታ ቀርቦ ነበር። ለዚህ ቦታ በካሬ ሜትር ቦታ 215,000 ብር በማቅረብ እና በቅድሚያ 40 በመቶ ለመክፈል በመስማማት ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው እውቀት ትሬዲንግ የተባለ ድርጅት ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ባለፈው ግንቦት ወር ባካሄደው ሁለተኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ፤ በፒያሳ አካባቢ ለሚገኙ ቦታዎች በካሬ ሜትር የቀረበው ከፍተኛ ዋጋ 350 ሺህ ብር ነበር። ይህን ዋጋ የከተማይቱ መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ባወጣው ጨረታ ላይ ያስገባው አዋሽ ባንክ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።
በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አቅራቢያ ካሉ የፒያሳ አካባቢዎች ውስጥ በሁለተኛው ዙር ለጨረታ የቀረቡት 22 ነበሩ። በእነዚህ ቦታዎች ላይ በሲኒማ አምፒር አቅራቢያ እንዳሉት ሁሉ መገንባት የሚቻለው፤ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ባለ አምስት ወለል ህንጻዎችን ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)