በቤርሳቤህ ገብረ
የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር በሐረር ከተማ የታሸጉ 35 የባንክ ቅርንጫፎች ተከፍተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲደረግ ለሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቤቱታ አቀረበ። የክልሉ መንግስት ቅርንጫፎቹ የታሸጉት “ግንባታቸው ባላለቁ ህንጻዎች አገልግሎት እየሰጡ በመሆኑ ነው” ቢልም፤ ማህበሩ ግን ከሌሎች የንግድ ድርጅቶች በተለየ መልኩ እርምጃው በእነርሱ ላይ መወሰዱ ለክልሉ የኮሪደር ልማት የተጠየቀው መዋጮ ተግባራዊ ባለመደረጉ ምክንያት የተፈጸመ እንደሆነ “ከድምዳሜ ላይ እንዲደርስ” እንዳደረገው ገልጿል።
በሀረሪ ክልል የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ባንኮች የሁለት ሚሊዮን ብር “ድጋፍ” እንዲያደርጉ በደብዳቤ የተጠየቁት የዛሬ ሶስት ሳምንት ገደማ ነው። ደብዳቤውን ለባንክ ቅርንጫፎች የጻፈው የሀረሪ ክልል የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ፤ የገንዘብ መጠኑን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ገቢ እንዲያደርጉ ቀነ ገደብ ሰጥቷቸው ነበር።
ሃያ ስድስት ባንኮችን በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር፤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ታህሳስ 9፤ 2017 ለሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በጻፈው ደብዳቤ፤ የባንክ ቅርንጫፎች የተጠየቁትን ያህል የገንዘብ መጠን በመዋጮ መልክ ለመክፈል “ስልጣን እንደሌላቸው” ገልጿል። የገንዘብ መዋጮ ጥያቄው በባንኮቹ “ዋና መስሪያ ቤት ታይቶ” እንዲሁም “በቂ በጀት የተመደበለት መሆኑ ተረጋግጦ” የሚፈቀድ መሆኑንም ማህበሩ አመልክቷል።
ክልሉ ያቀረበው ጥያቄ ለየባንኮቹ ዋና መስሪያ ቤት ተልኮ እየታየ ባለበት ወቅት፤ የሐረር ከተማ አስተዳደር 35 የባንክ ቅርንጫፎችን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እንዲታሸጉ ማድረጉን ማህበሩ አስታውቋል። እርምጃው የተወሰደባቸው ምክንያቶች በሚል ለባንክ ቅርንጫፎቹ በቃል ከተነገራቸው ውስጥ “ግንባታው ያላለቀ ህንጻ ውስጥ መስራት አትችሉም” የሚለው እንደሚገኝበት “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው ደብዳቤ ላይ ተጠቅሷል።
ባንኮቹ ቅርንጫፎቹን የከፈቱባቸው ህንጻዎች “የግንባታ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው” የሚለው ሌላኛው በምክንያትነት የተነሳ ጉዳይ እንደሆነ ማህበሩ ገልጿል። የህንጻዎቹ ባላቤቶች “የአከራይ እና ተከራይ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው” የሚሉትም እንዲሁ ለባንክ ቅርንጫፎቹ በቃል ከተነገራቸው ምክንያቶች ውስጥ እንደሚገኝበት የማህበሩ ደብዳቤ አትቷል።
እነዚህን ምክንያቶች መሰረት አድርጎ በባንክ ቅርንጫፎቹ ላይ የተወሰደው የእግድ እርምጃ “በተመሳሳይ ህንጻ ውስጥ እየሰሩ የሚገኙ ሌሎች ንግድ ድርጅቶችን ያልተመለከተ” መሆኑን ማህበሩ በማነጻጸሪያነት አንስቷል። የንግድ ድርጅቶቹ በአሁኑ ወቅት ስራቸውን “ያለምንም እንከን እያከናወኑ ይገኛሉ” ያለው ማህበሩ፤ እርምጃው የባንክ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለይቶ ተግባራዊ መደረጉ “ለኮሪደር ልማቱ የተጠየቀው መዋጮ ተግባራዊ ባለመደረጉ ምክንያት የተፈጸመ እንደሆነ ከድምዳሜ ላይ እንድንደርስ አድርጎናል” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።
የሀረሪ ክልል የኢንተርፕራይዝ ልማት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢስማኤል ዩሱፍ፤ በባንክ ቅርንጫፎቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ ከኮሪደር ልማት መዋጮ ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የባንክ ቅርንጫፎቹ “መዋቅሩ ተሰርቶ ያላለቀ” ህንጻ ላይ ባንኮች ተከራይተው እንደሚገቡ እና “ከላይ ግንባታ መሰራቱ ትክክል አለመሆኑን” ኃላፊው አስረድተዋል።
“ከባንኩ ጋር የሚያገናኘን ነገር የለም ከባለሀብቱ ነው። መሬት በኢንቨስትመንት የወሰደው ከሱ ጋር ተነጋግረን እኛ በሶስት ወር አስተካክላለው አጠናቅቃለሁ የሚል በጽሁፍ የሰጠነው አለ። ባለሀብቱ ላይ እርምጃ እንወስዳለን። አገልግሎት መስጠት አይችልም። ባንኩ ያለው ውል ከባለሀብቱ ጋር ነው። ባንኮቹ አማራጭ መፈለግ ይችላሉ” የሚሉት አቶ ኢስማኤል፤ በዚህም መሰረት ባንኮች ግንባታው የተጠናቀቀ ህንጻ ላይ ለቅርንጫፎቻቸው ቢሮ መከራየት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
መስሪያ ቤታቸው ከሶስት ወራት በፊት ባላለቁ ህንጻዎች ላይ ያሉ ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎችን ጭምር ሲያሽግ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል። የህንጻዎቹ ባለቤቶች የግንባታ ማጠናቀቂያ ስራ “በአንዴ የሚያልቅ” ባለመሆኑ፤ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ምን ያህሉን የህንጻ ክፍል መገንባት እንደሚችሉ ለቢሮው በፈርማ መተማመኛ መስጠታቸውንም ገልጸዋል። ቢሮው ከወራት በኋላ ባደረገው ግምገማ፤ ቃል የተገባባቸው ስራዎች ባለመሰራታቸው ወደ ማሸግ እርምጃ መግባቱን አቶ ኢስማኤል አብራርተዋል።
የሀረሪ ክልል የኢንተርፕራይዝ ልማት እና ኢንዲስትሪ ቢሮ ኃላፊ በሐረር ከተማ አሁንም ያልታሸጉ ብዙ የባንክ ቅርንጫፎች እንዳሉ ቢገልጹም፤ የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር ግን የማሸግ እርምጃው “አሉታዊ ውጤት” “በሐረር ከተማ ብቻ ሳይወሰን ለሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ተርፏል” ሲል በአቤቱታ ደብዳቤው ላይ አስፍሯል። ባንኮች የፋይናንስ ተቋም ከመሆናቸው አንጻር “በደንበኞች እና የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዲፈጠር አድርጓል” ብሏል ማህበሩ።
በሀረሪ ክልል በባንክ ቅርንጫፎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ ባለፈው ሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገው የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር፤ እርምጃውን “ፈጽሞ ትክክል ያልሆነ” ነው ሲል ጠርቶታል። የታሸጉት የባንክ ቅርንጫፎች “ህጋዊ ውል ተዋውለው ስራቸውን ለረጅም ጊዜ ማከናወናቸውን” እና ከኪራይ ክፍያ በተጨማሪም ለመንግስት መከፈል ያለበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ “በአግባቡ መክፈላቸውን” ማህበሩ አስታውሷል።
ቅርንጫፎቹ “አንድም ቀን በግልጽ በአደባባይ ስራዎቻቸውን ሲያከናውኑ፤ ‘ህንጻው የመጠቀሚያ ፈቃድ የለውም፤ መስራት አትችሉም ተብሎ የደረሳቸው ማስጠንቀቂያ የለም” ያለው ማህበሩ፤ “በድንገተኛ ትእዛዝ” እንዲዘጉ መደረጉ የዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን “ማስተጓጉሉን” አመልክቷል። የቅርንጫፎቹ መዘጋት “እንደ ሀገር የስም መጉደፍ” ማስከተሉን እና “የገቢ ማጣት እያስከተለና የፋይናንስ ፍሰቱን” እየጎዳ እንደሚገኝም ማህበሩ አክሏል።
“ያለምንም ህጋዊ መሰረት የሚወሰድ እርምጃ በኢኮኖሚው ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ንቁ ተዋናዮችን የሚጎዳ እንዲሁም አዲስ የውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢኮኖሚው እንዳይቀላቀሉ እንቅፋት የሚሆን አካሄድ ነው። ይህም ተግባር ሀገራችን የያዘችውን የግል ሴክተሩን የማበረታት እና የኢኮኖሚው ዋና ተዋናይ እንዲሆን የማድረግ አካሄድን የሚጎዳ ነው” ሲል ማህበሩ በደብዳቤው አትቷል።
በኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ፊርማ ለሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የተላከው ይህ ደብዳቤ፤ የባንኮች የማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት “ፈቃደኝነት” እና “አቅምን መሰረት ያደረገ” ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል። “ባንኮች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚሰሩ በመሆናቸው፤ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በብዙ ቦታ በተቀናጀ መልኩ መወጣት ያለባቸው መሆኑ ታሳቢ መደረግ” እንደሚገባው የገለጸው ማህበሩ፤ ለወደፊቱ መሰል የሆኑ የመዋጮ ጥያቄዎች ሊቀርብላቸው የሚገባው በዋናው መስሪያ ቤታቸው በኩል መሆን እንደሚገባው አስገንዝቧል።
በባንክ ቅርንጫፎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ኢንዱስትሪው እና የሀረሪ ክልል የነበራቸውን “መልካም ልማታዊ የስራ ግንኙነት የሚያበላሽ” እንደሆነ በደብዳቤው ላይ አጽንኦት ሰጥቷል። በክልሉ እየተወሰደ ያለው የባንክ ቅርንጫፎችን የማሸግ እና አገልግሎት እንዳይሰጡ የማድረግ እርምጃ “እንዲቆም” እና ቅርንጫፎቹ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲቀጥሉ ማህበሩ በደብዳቤው ጠይቋል።
“ያለምንም ህጋዊ መሰረት የሚወሰድ እርምጃ በኢኮኖሚው ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ንቁ ተዋናዮችን የሚጎዳ እንዲሁም አዲስ የውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢኮኖሚው እንዳይቀላቀሉ እንቅፋት የሚሆን አካሄድ ነው”
– የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር
የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር በአቤቱታ ደብዳቤው ማጠቃለያ፤ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር “ጉዳዩን በጥሞና አይተው” እንደሚያስተካክሉ ያለውን “ጽኑ እምነትም” ገልጿል። የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጃሚ አህመድ የማህበሩ ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው ሆኖም ክልሉ ለውይይት ክፍት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)