ከመተሐራ ከተማ አቅራቢያ ዛሬ ምሽት የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

ከመተሐራ ከተማ አቅራቢያ 13 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ዛሬ ሰኞ ምሽት የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ የተሰማው የዛሬው ምሽት ርዕደ መሬት፤ በሬክተር ስኬል 4.9 የተመዘገበ መሆኑን መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአካባቢው ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተ ነው። ትላንት ለሊት 10 ሰዓት ከ13 ደቂቃ አካባቢ፤ ከአዋሽ ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ስፍራ ተመሳሳይ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ እንደነበር በመላው ዓለም የደረሱ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶችን የሚመዘግቡ ተቋማት ያወጧቸው መረጃዎች አመልክተው ነበር። 

የትላንት ለሊቱ የመሬት መንቀጥቀጡን የመዘገቡ እነዚሁ ተቋማት፤ መጠኑ መጠነኛ የሚባል እና በሬክተር ስኬል 4.6 የሚለካ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል። ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 14፤ 2017 ምሽት 4 ሰዓት ከ40 ገደማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ በአዋሽ አካባቢ ከተመዘገበው ርዕደ መሬት ጋር በመጠን እኩል ነው።

በአፋር ክልል የሚገኘው የአዋሽ አካባቢ፤ ባለፈው መስከረም እና ጥቅምት ብቻ 10 የመሬት መንቀጥቀጦችን አስተናግዷል። በአካባቢው እስካሁን የተመዘገበው ከፍተኛ የርዕደ መሬት መጠን፤ በሬክተር ስኬል 4.9 የተለካ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)