በቤርሳቤህ ገብረ
በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ወንዞችን፤ በባህሪያቸው “አደገኛነት” ባላቸው ደረቅም ይሁን ፈሳሽ ቆሻሻ የሚበክሉ ድርጅቶችን አንድ ሚሊዮን ብር ቅጣት የሚጥል ደንብ ተግባራዊ ሊደረግ ነው። ከመኖሪያ ቤቶች የሽንት ቤት አሊያም ማንኛውንም ያልተጣራ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ መልቀቅ እስከ 300 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ደንቡ ይደነግጋል።
የወንዞችን ብክለት ለመከላከል የሚያስችለውን ይህ ደንብ የጸደቀው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባለፈው ታህሳስ ወር ባደረገው ስብሰባ ላይ ነው። በደንቡ ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎች ከታህሳስ 2፤ 2017 ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ በሰነዱ ላይ ቢገልጽም፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በዚህ መሰረት ገና መቅጣት አለመጀመሩን የመስሪያ ቤቱ ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከከተማይቱ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን፤ ደንቡን የተመለከተ ስልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ በትላንትናው እና በዛሬው ዕለት አካሄዷል። በዚህ ስልጠና ላይ ደንቡን የሚያስተገብሩ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ አመራሮች እንደዚሁም የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እና የከተማይቱ የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በስልጠናው “የወንዝና ወንዝ ዳርቻን ስለማልማት እና ከብክለት ስለመከላከል፣ ስለ ተከለከሉ ተግባራት እና ስለቅጣት ዓይነቶች” ገለጻ መደረጉን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። ስልጠናው የተመረኮዘበት “የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ”፤ በሰባት ክፍሎች እና በ21 አንቀጾች የተከፋፈለ ነው።
በእነዚህ ክፍሎች ከተዘረዘሩት ውስጥ ስለ ተከለከሉ ተግባራት፣ ስለ ተቋማት ተግባርና ኃላፊነት፣ ጥቆማ እና አቤቱታ ስለማቅረብ እንዲሁም ስለ አስተዳደራዊ እርምጃ አወሳሰድ የተመለከቱ ድንጋጌዎች ይገኙበታል። በደንቡ መጨረሻ በአባሪነት የተካተተው ሰንጠረዥ፤ በወንዝ እና በወንዝ ዳርቻ ላይ ብክለት በሚፈጸሙ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ላይ የሚጣሉ አስተዳደራዊ የገንዘብ ቅጣቶችን ዘርዝሯል።
ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ አካላት የሚጣለው ቅጣት ከሁለት ሺህ ብር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ ቅጣት ይጣልባቸዋል። ዝቅተኛው የሁለት ሺህ ብር ቅጣት የተጣለው፤ በወንዝ እና በወንዝ ዳርቻ ክልል ውስጥ በሚጸዳዱ ግለሰቦች ላይ እንደሆነ በደንቡ ላይ ተመልክቷል። በደንቡ ከተካተቱ ቅጣቶች በገንዘብ መጠኑ ከፍተኛ የሆነው የአንድ ሚሊዮን ብር ቅጣት የሚጣለው ደግሞ፤ “በባህሪው አደገኛነት ያለው ደረቅም ይሁን ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ መጣል ወይም እንዲጣል በማድረግ በሚበክሉ ድርጅቶች ላይ ነው።

ይህ የደንብ ጥሰት በግለሰብ ደረጃ ተፈጽሞ የሚገኝ ከሆነ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በደንቡ ላይ ሰፍሯል። በደንቡ የሰፈሩ ስድስት የጥፋት አይነቶችን የሚፈጽሙ ድርጅቶች እና የሰፈሩ ግለሰቦች፤ ለእያንዳንዱ ጥፋት 400 ሺህ ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።
አራት መቶ ሺህ ብር ከሚያስቀጡ ጥፋቶች አንዱ፤ የፍሳሽ ማጣሪያ ሳይኖር በወንዝ ዳርቻ እና አካባቢ ላይ የተሽከርካሪ እጥበት ማከናወን ነው። ከጤና እና ከትምህርት ተቋማት፣ ከነዳጅ ማደያ፣ ከጋራዦች እና ከመኪና ማጠቢያዎች የሚወጡ የተለያዩ በካይ ኬሚካል ፍሳሽ ቆሻሻዎችን፤ በወንዝና ወንዝ ዳርቻ ላይ ማከማቸት፣ መጣል ወይም መልቀቅም እንዲሁ 400 ሺህ ብር ያስቀጣል።
ማንኛውም በካይ ፍሳሽ ከተፈቀደው የፍሳሽ ማጠራቀሚያ ውጭ፤ በፍሳሽ መስመር አሊያም ከጎርፍ መውረጃ ቦይ ጋር በማገናኘት ወደ ወንዝና ወደ ወንዝ እና ወንዝ ዳርቻ እንዲፈስ ማድረግ በተመሳሳይ 400 ሺህ ብር ቅጣት ያስከትላል። በራሱ ወይም ከሌላ ንጥረ ነገር ጋር ሲዋሃድ መርዛማ ኬሚካል በማመንጨት በወንዙ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ፍሳሽ የሚለቅ አካል እንደዚሁ 400 ሺህ ብር ቅጣት በደንቡ ተጥሎበታል።

በወንዝ ውሃ ላይ የሚፈነዳ ወይም መርዛማና አደገኛ ጋዝ ትነት የሚያመነጭ ፍሳሽ የሚለቅ አካልም ተመሳሳይ የገንዘብ መጠን ያለው ቅጣት ይጠብቀዋል። ዘይት፣ ጨዋማ ፈሳሽ፣ የተቀጣጠለ የሞተር ዘይት፣ ነዳጅ ወይም ሳሙና ነክ የሆኑ እና ሊሎች የወንዙን ውሃ ተፈጥሯዊ ይዘት ሊቀይሩ የሚችሉ ነገሮች የያዘ ፍሳሽ መልቀቅ 400 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ደንቡ ያመለክታል።
ከመኖሪያ ቤት የሽንት ቤት ወይም ማንኛውም ያልተጣራ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ መልቀቅ ወይም መስመሩን አገናኝቶ ወንዙን መበከል እስከ 300 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚኖረውም ደንቡ ይደነግጋል። የሽንት ቤት ፍሳሽ የማስወገድ ፈቃድ ያለውም ሆነ ፈቃድ ሳይወስድ የሚሰራ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት በሚያስወግድበት ጊዜ ቀጥታ ወደ ወንዝ የሚደፋ ወይም የሚቀላቅል ከሆነ በደንቡ መሰረት 100 ሺህ ብር ቅጣት ይከፍላል።
በወንዝና በወንዝ ዳርቻ ውስጥ ከተፈቀደው የመዝናኛ፣ መናፈሻ፣ ፓርክ እና ሌሎች ለወንዝ ዳርቻው ልማት አስፈላጊ ከሆነ ግንባታ ውጭ የፕላስቲክ ቤት ወይም ማንኛውም ዓይነት ግንባታ መገንባት 200 ሺህ ብር ቅጣት ያስከትላል። በወንዝ ዳርቻ ክልል ውስጥ እንስሳት ማሰማራት ወይም እንዲገቡ ማድረግ እንደዚህም ከተፈቀደ መግቢያና መውጫ ውጭ ተሸከርካሪ ማሽከርከር 30 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በደንቡ ላይ ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)