በኢትዮጵያ ከሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የ47 በመቶው መንስኤ “ዛፎች የሚፈጥሩት ንክኪ ነው” ተባለ   

በቤርሳቤህ ገብረ

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ 47 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው፤ ዛፎች እና ቅርንጫፎች በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ የሚፈጥሩት ንኪኪ መሆኑ ተገለጸ። በመሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ስርቆቶች እና ጉዳቶች የኃይል መቆራረጥ እንዲከሰት የሚያደርጉ ሌሎች ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውንም ተነግሯል።

ይህ የተገለጸው፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ መስመሮችን የማስተዳደር እና የኤሌክትሪክ ኃይልን በጅምላ ገዝቶ ለደንበኞች የመሸጥ ኃላፊነት ያለፈበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፤ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 20፤ 2017 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት፤ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌቱ ገረመው እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ ናቸው።

ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በስሩ ከሚገኙ እና ከሚያስተዳድራቸው የመንግስት ልማት ድርጅቶች አንዱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ነው። ይህን ተቋም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመሩት የቆዩት አቶ ሽፈራው ተሊላ፤ ምክትላቸው በነበሩት አቶ ጌቱ ገረመው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተተክተዋል። 

አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የተቋሙን የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል። ተቋሙ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና ጥራትን እንዲሁም የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥን እንዴት ለማሻሻል እንዳቀደም አብራርተዋል።

የኃይል አቅርቦት እና ጥራትን ለማሻሻል ድርጅቱ በአጭር ጊዜ ለመተግበር ካቀዳቸው ተግባራት መካከል፤ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ውስጥ የገቡ ዛፎች እና ቅርንጫፎችን መቁረጥ አንዱ ነው። ተቋሙ ከመዘገባቸው የኃይል መቆራረጦች ውስጥ 47 በመቶ መሆኑ የሚደርሰው በዛፎች እና ቅርንጫፎች አማካኝነት መሆኑም በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። 

በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ አደጋ የሚፈጥሩ ዛፎች እና ቅርንጫፎችን የመቁረጥ ተግባር ከሁለት ወር በፊት እንደተጀመረ የገለጹት አቶ ጌቱ፤ የስራው አፈጻጸም በአዲስ አበባ 50 በመቶ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ 30 በመቶ እንደደረሰ አስረድተዋል። ተቋሙ ቀሪዎቹን ስራዎች፤ ባወጣው የ100 ቀናት እቅድ ውስጥ ለመጨረስ ከሰራተኞቹ ጋር መግባባት ላይ መድረሱንም አክለዋል።  

“አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንዳያችሁት በጣም ብዙ ዛፎች ተቆርጠዋል። ያም የሆነበት ምክንያት ለብዙ [የኃይል] መቆራረጥ መንስኤ ስለነበሩ ነው። ከእንግዲህ ወይ አጫጭር ዛፎች መተከል አለባቸው አለበለዚያ [ዛፎቹ] በሶስት ሜትር ርቀት ላይ መሆን እንዳለባቸው ህዝቡም እንዲገነዘብ እፈልጋለሁ” ሲሉ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተናግረዋል።

ለኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ “ትልቅ ምክንያቶች ናቸው” በሚል በአቶ ጌቱ የተጠቀሱት ሌሎች ጉዳዮች፤ በመሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ስርቆቶች እና ጉዳቶች ናቸው። “ሰሞኑን አስተውላችሁ ከሆነ በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል አምቦ፣ ጎንደር፣ ወልዲያ እና ኮምቦልቻ አካባቢ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንብረቶች ወድመውብናል። በዚያ ምክንያት ህዝቡም ጭለማ ውስጥ ለሶስት ለአራት ቀን መልሰን እስክናገናኝ የመቆየት ሁኔታዎች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር ንግግሮች መጀመራቸውን የገለጹት አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸዋል። የተቋሙ ኃላፊዎች ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ከአምስት የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር መገናኘታቸውን ያመለከቱት አቶ ጌቱ፤ በቀጣይም ተቋሙ ከፌደራል ፖሊስ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን ጥቆማ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)