የታላቁ የህዳሴ ግድብ በስድስት ወራት ውስጥ ሊመረቅ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ

የግንባታ ስራው እየተጠናቀቀ እንደሆነ የተነገረለት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፤ በስድስት ወራት ውስጥ ሊመረቅ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፍንጭ ሰጡ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በጉባ ወረዳ በመገንባት ላይ የሚገኘው ይኸው ግድብ፤ በአሁኑ ወቅት 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዙንም አብይ ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ህዳሴው ግድብ የመጠናቀቂያ ጊዜ ፍንጭ የሰጡት፤ አቶ መሐመድ አህመድ ቆጴ የተባሉ የፓርላማ አባል ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው። ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 11፤ 2017 በተካሄደው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ፤ አቶ መሐመድ “የህዳሴውን ግንባታ ሙሉ በሙሉ አጠናቀን ሪቫን ለመቁረጥ ምን ያህል ርቀት ይቀረናል?” ሲሉ ጠይቀዋል።  

የህዳሴውን ግድብ “ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮጀክት” ሲሉ የጠሩት አቶ መሐመድ፤ ግድቡን “የኢትዮጵያ ህዝብ በላቡ እና በደሙ እየገነባው” እንደሚገኝ ተናግረዋል። “በዓለም ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታዎች” ግንባታውን ለማጠናቀቅ እና ከግድቡ ጋር በተያያዘ የሚካሄዱ ንግግሮችን “ከመቋጨት አኳያ” የሚኖራቸውን አንድምታ አስመልክቶ የፓርላማ አባሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፤ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ አሁንም “ለውይይት እና ለንግግር”  ፍላጎት ያላት መሆኑን አስረድተዋል። የህዳሴው ግድብ “የአፍሪካ ኩራት” መሆኑን የገለጹት አብይ፤ ግብጽ ግድቡ አሁን “ያለበትን ሁኔታ ለማየት” ከፈለገች ኢትዮጵያ ለማስተናገድ “ክፍት” መሆኗን አብራርተዋል። 

ግድቡን በተመለከተ “ለፕሬዝዳንት ሲሲ ካይሮ ላይ ቃል ገብተህ ነበር” የሚል ክስ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያቀርቡባቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለግብጹ ፕሬዝዳንት በወቅቱ የተናገሩት “ህዳሴው ሲሞላ አንድ ሊትር ውሃ እንኳን ከአስዋን ግድብ አይጎልም” የሚል እንደነበር ለፓርላማ አባላቱ አስታውሰዋል። 

“አሁን ህዳሴ መቶ ፐርሰንት ሞልቷል” ያሉት አብይ፤ ግብጽ በናይል ወንዝ ላይ የገነባችው አስዋን ግድብ በተመሳሳይ መቶ ፐርሰንት ሙሉ በመሆኑ “ቃሉ ተፈጽሟል የተካደ ነገር የለም” ሲሉ ራሳቸውን ተከላክለዋል። የቀድሞውን የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የደህንነት ሹም ከአንዴም ሁለቴ ባነጋገሩበት ወቅት “ህዳሴ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብጽ ላይ የተለየ ችግር የሚያመጣ” አለመሆኑን እንዳስረዷቸውም ጠቅሰዋል።

“‘የእኛ አላማ ኢነርጂ ማምረት ነው፤ እናንተን መጉዳት እኛ አንፈልግም’ ስላቸው ስጋታቸው ድርቅ እንደሆነ አነሱልኝ። ድርቅ ቢያጋጥመን የሚል ስጋት አነሱ። ድርቅ እኮ ያጋጥማል የሚባለው ኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ ደርቆ ግብጽ ቢዘንብ ዋጋ የለውም፤ የአባይ ውሃ ከዚህ ስለሚሄድ። ግብጽ ድርቅ ኖሮ ኢትዮጵያ ደሞ ዝናብ ካለ፤ ውሃው ሁሌም አለ ማለት ነው። ድርቅ እንዳይኖር መከላከል ያለብን እዚህ ነው። ውሃው በበቂ እንዲሄድ” ሲሉ የሁለቱ ሀገራት ዕጣ ፈንታ የተሳሰረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። 

ኢትዮጵያ “አረንጓዴ አሻራን” እና “cloud seeding” በመጠቀም የዝናብ መጠን እንዲጨምር የምታደርገውን ጥረት በማንሳት “ጉዳት እንደማይደርስባቸው” ለግብጽ ባለስልጣናት ማስተማመኛ ለመስጠት እንደሞከሩም አብይ በዛሬው ማብራሪያቸው አንስተዋል። “ ‘በዚህ መንገድ መንግስታችሁን አሳምናችሁ በትብብር እንስራ’ የሚል ፕሮፖዛል በተደጋጋሚ ቀርቦላቸዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የግብጽ ባለስልጣናት “በወጉ ስራቸውን ሰርተው ቢሆን ኖሮ የተሻለ ትብብር መፍጠር ይቻል ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል። 

“አሁንም ከግብጽ ወንድሞቻችን ጋር በውይይት ይበልጥ አብረን መስራት መደጋገፍ እንዳለብን እናምናለን። የሚያጣላን፣ የሚያጨቃጭቀን፣ ገንዘባችንን እዚያ እና እዚህ የሚያስበትነን ጉዳይ አለ ብለን አናምንም”

– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር ድርድር ስታደርግ ብትቆይም፤ ሂደቱ ከታህሳስ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋርጧል። “አሁንም ከግብጽ ወንድሞቻችን ጋር በውይይት ይበልጥ አብረን መስራት መደጋገፍ እንዳለብን እናምናለን። የሚያጣላን፣ የሚያጨቃጭቀን፣ ገንዘባችንን እዚያ እና እዚህ የሚያስበትነን ጉዳይ አለ ብለን አናምንም። በትብብር አብረን ብንሰራ፤ ሁለቱ ህዝቦች ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ” ብለዋል አብይ።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ “አንድ ብር እርዳታም ሆነ ብድር ከውጭ ያልተገኘበት” መሆኑን ለፓርላማ አባላቱ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ብዙ ፈተና አይተንበታል” ሲሉ ተደምጠዋል። የግንባታ ግብዓቶች ተገዝተው ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ግድቡ እስካለበት ስፍራ ድረስ ማድረስ፤ ከውጪ ጫና ጋር ተደማምሮ “በጣም አስቸጋሪ” እንደነበርም አብይ አስረድተዋል። 

“ህዳሴ ላይ ብዙ መከራ ታይቷል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ በመንፈቅ ጊዜ ውስጥ ሊመረቅ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል። ጥያቄውን ላቀረቡት የፓርላማ አባልም “ቢበዛ በሚቀጥሉት 6 ወራት በጋራ ሪቫን እንቆርጣለን” ሲሉ አረጋግጠውላቸዋል። “ይሄን ጊዜ የምንወስድበት ምክንያት ዝግጅት ስለሚፈልግ እና አካባቢው ሞቃታማ ስለሆነ የክረምቱን ዝናብ ስለምንፈልገው ብቻ [ነው]” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “በሚቀጥለው ዓመት መጀመርያ አካባቢ ታሪክ ይሆናል” ያሉት የህዳሴው ግድብ ግንባታ፤ 14 ዓመታት ገደማን ወስዷል። ለግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተጣለው መጋቢት 24፤ 2003 ዓ.ም. ነበር። 

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታው ሲጀመር 5,250 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳለው በወቅቱ ተነግሮ ነበር። ግድቡ ይመረቃል ከተባለበት ወራት አስቀድሞ፤ ኢትዮጵያ ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል 50 በመቶ ገደማ ድርሻ መያዙን  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፈው ታህሳስ ወር አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)