በብርቱካን ዋልተንጉስ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ አራት ዞኖች ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በተከሰተ የእንስሳት በሽታ ወረርሽኝ፤ ከ1,400 በላይ ከብቶች መሞታቸውን የአካባቢው የስራ ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በክልሉ የሚገኙ 6,500 የሚሆኑ ከብቶች የበሽታው ምልክት እንደታየባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል።
ከጋሞ ዞን ወደ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ እና አሌ ዞኖች የተዛመተው የእንስሳት በሽታ ወረርሽኝ፤ በዋናነት የሚያጠቃው በሬዎችን እና ላሞችን ነው። በወረርሽኙ የተጠቁ ከብቶች፤ ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት፣ የመተንፈሻ አካላት ጭንቀት እና ሳል፣ ከአፍንጫቸው ውሃ የሚመስል ፈሳሽ መውጣት እና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ምልክቶች ይታዩባቸዋል።
ምንነቱ እስካሁን በምርመራ ያልታወቀው ይህ የእንስሳት በሽታ፤ በከብቶች ጭንቅላት እና ትከሻቸው አካባቢ እብጥት ያስከትላል። “የከብቶችን አቅም በማዳከም በፍጥነት እንደሚገድል” የሚነገርለት ይህ በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ በታየበት በጋሞ ዞን ጋርዳ ማርታ ወረዳ ብቻ 693 ከብቶች ባለፉት አምስት ቀናት ውስጥ መሞታቸውን የወረዳው ግብርና መምሪያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

የጋርዳ ማርታ ወረዳ የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ሀሼ፤ በሽታው “በፍጥነት የሚዛመት” እንደሆነ አስረድተዋል። የአካባቢው አርብቶ አደሮች ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ምክንያት፤ በሽታው ወደ ጎፋ ዞን ተዛምቶ 216 ከብቶች መሞታቸውን የዞኑ የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በጎፋ ዞን ወረርሽኙ የተከሰተባቸው ዑባ ደብረ ጸሀይ እና ዛላ የተባሉት ወረዳዎች መሆናቸውንም ኃላፊው ጠቁመዋል። እንደ ጎፋ ዞን ሁሉ በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ እስካሁን ወረርሽኙ የታየው በሁለት ወረዳዎች ላይ ነው። በወረርሽኙ ሳቢያ በዞኑ ባሉት በማሌ እና በናጸማይ ወረዳዎች ከ500 በላይ ከብቶች መሞታቸውን የደቡብ ኦሞ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ንጉሴ ማቴዎስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በጋሞ፣ ጎፋ እና በደቡብ ኦሞ ዞኖች ውስጥ 6,500 የሚሆኑ ከብቶች የበሽታው ምልክት እንደታየባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር አዲሱ ኢዮብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የእንስሳት ወረርሽኙ ከሶስቱ ዞኖች በተጨማሪ በትላንትናው ዕለት ወደ አሌ ዞን እንደተዛመተ መረጋገጡንም አክለዋል።

በበሽታው ለሚጠቁ ከብቶች ህክምና ከመስጠት ጎን ለጎን የበሽታውን አይነት ለመለየት በክልሉ የሚገኙ የላብራቶሪ ባለሙያዎች ቦታው ድረስ በመሄድ ናሙና ወስደው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አመልክተዋል። የክልል እና የዞን ባለሙያዎች፤ በሽታው የተከሰተበት ቦታ ድረስ እንዲሄዱ እና እንዲደግፉ መደረጉንም ዶ/ር አዲሱ ጨምረው ገልጸዋል።
ለከብቶች የሚሆኑ ተጨማሪ ክትባቶች እና መድኃኒቶች “ከግብርና ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲደረግ እና በክልል መንግስት በኩልም ደግሞ ድጋፍ ተደርጎ ግዢ እንዲፈጸም የማድረግ ስራ መሰራቱን” የቢሮው ምክትል ኃላፊ አብራርተዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወረርሽኙ ምልክት ከታየባቸው ከብቶች መካከል 5,500 ያህል የሚሆኑት ህክምና ተደርጎላቸው መዳናቸውን ዶ/ር አዲሱ ጠቁመዋል።
በበሽታው ያልተያዙ ከብቶች ለወረረሽኙ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ክትባት እንዲሰጣቸው መደረጉን የክልሉ የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ገልጸዋል። ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በበሽታው ምክንያት “የተወሰኑ” ከብቶች መሞታቸውን ተከትሎ፤ ከቦታ ቦታ የሚደረግ የከብቶች “እንቅስቃሴ እንዲቆም” ትዕዛዝ መተላለፉንም ዶ/ር አዲሱ አክለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ በከብቶች ላይ የተጣለው ይህ የእንቅስቃሴ ገደብ፤ የበሽታው ስርጭት ባለበት እንዲገታ አድርጎታል ባይ ናቸው። በበሽታው የሞቱ ከብቶች ብዛት ከትላንት በስቲያ “መለስተኛ” እንደነበር ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል።
ሁኔታው በትላንትናው ዕለት መሻሻል በማሳየት፤ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች “ሙሉ በሙሉ” ሞት አለመከሰቱን ምክትል የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል። በክልሉ በበሽታው ሳቢያ ምን ያህል ከብቶች እንደሞቱ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር አዲሱ፤ “የሞት መረጃ አላደራጀንም። ገና እየተደራጀ ነው። የታመሙት እንስሳት እንዳይሞቱ የመከላከል ስራን ነው ቅድሚያ የሰጠነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)