የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ዕጩዎችን እንዲጠቁም ለትግራይ ህዝብ ጥሪ ቀረበ 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ብቁ የሚሆኑ ዕጩዎችን እንዲጠቆሙ ለክልሉ ህዝብ ጥሪ  አቀረቡ። ዕጩዎቹ “የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስራዎች በብቃት የሚያከናውኑ” እንዲሁም “የክልሉን ሰላም እና ደህንነት ማረጋገጥ የሚችሉ መሆን” ይገባቸዋል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ጥሪ ያቀረቡት፤ ለመላው የትግራይ ህዝብ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው በዛሬው ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት ነው። በትግርኛ ቋንቋ የተጻፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት፤ “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጥቆማ ጥሪ” በሚል ርዕስ የቀረበ ነው።

አብይ በዚሁ መልዕክታቸው፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሲቋቋም መሰረት ያደረገው አዋጅ ለአስተዳደሩ የሚፈቅደው የስራ ዘመን “ሁለት ዓመት ብቻ” እንደሆነ አስታውሰዋል። ሆኖም “ተጨባጭ ምክንያት ካለ” የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዕድሜ ሊራዘም እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ጉዳይ ለማስረዳት በመልዕክታቸው የጠቀሱት፤ የፌደራል መንግስት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ በ1995 ዓ.ም የወጣውን አዋጅን ነው። አዋጁ “በአንድ ክልል ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት ከተፈጸመ”፤ የፌደራል መንግስት “የክልሉን ምክር ቤት እና የክልሉን ከፍተኛ የህግ አስፈጻሚ አካል በማገድ ለፌደራል መንግስቱ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም” ሊወሰን እንደሚችል ይደነግጋል። 

በዚሁ አዋጅ መሰረት “ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የሚቆየው ከሁለት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ነው።” ሆኖም “አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመቆያ ጊዜውን ከ6 ወር ላልበለጠ ጊዜ ለማራዘም እንደሚችል” በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። ይህን አዋጅ እና በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የግጭት ማቆም ስምምነት መሰረት በማድረግ፤ በትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የሚያስችል ደንብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያጸደቀው መጋቢት 9፤ 2015 ነበር።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የስልጣን ዘመን ምን ያህል እንደሚሆን በግልጽ ባያስቀመጥም፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በ1995ቱ አዋጅ የተሰጡትን ስልጣን እና ተግባራት እንደሚያከናውን ደንግጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዛሬው መልዕክታቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሊያከናውናቸው ከሚገባቸው “ቁልፍ ስራዎች” መካከል አንዱ “ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር” እንደነበር ገልጸዋል።



“ይህ ተግባር ካልተፈጸሙ ስራዎች መካከል አንዱ በመሆኑ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ዕድሜ በህግ በማሻሻል፤ በአንድ ዓመት ማራዘም የግድ ሆኖ ይገኛል” ሲሉ አብይ በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የስልጣን ጊዜ “ለአንድ ዓመት ሊራዘም እንደሚችል” የመጀመሪያውን ጥቆማ የሰጡት ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 11፤ 2017 በፓርላማ በነበራቸው የጥያቄ እና መልስ ቆይታ ወቅት ላይ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐሙሱ የፓርላማ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራ ከተገመገመ በኋላ፤ “በግለሰቦች ደረጃ ለውጥ ሊካሄድ እንደሚችልም” ተናግረዋል። “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተገምግሞ፣ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎ፤ የፕሪቶሪያን ስምምነት በሚያከብር መንገድ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ስራውን እየሰራ፣ ህዝቡን ለምርጫ ማዘጋጀት እና ህዝቡን የስልጣን ባለቤት የማድረጉን ሂደት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል” ሲሉም ቀጣይ ሂደቱ ምን ሊመስል እንደሚችል በዚሁ ማብራሪያቸው ላይ አመልክተዋል።

አብይ በዛሬው መልዕክታቸው “የፌደራል መንግስት መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ዕድሜ ለማራዘም ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና የህግ መሰረቶችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ” አስታውቀዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ “አዲስ” የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት መሾም “አስፈላጊ ሆኖ” መገኘቱንም በመልዕክታቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ከመጋቢት 14፤ 2015 ጀምሮ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ የሚገኙት አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሆኑ ይታወቃል። አቶ ጌታቸው የፕሬዝዳንትነት ሹመቱን ያገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አማካኝነት ነው። የትግራይ ክልል  ጊዜያዊ አስተዳደርን እንዲቋቋም ያደረገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ “ርዕሰ መስተዳድሩ [በፕሪቶሪያ] የሰላም ስምምነት መሰረት በሚደረግ የፖለቲካ ምክክር ተለይቶ፤ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾማል” ይላል።

በዚህ ድንጋጌ መሰረት የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት መሾም “የጠቅላይ ሚኒስትር ኃላፊነት መሆኑን” አብይ በዛሬው መልዕክታቸው ቢገልጹም፤ ስለ “ፖለቲካዊ ምክክር” ግን ያሉት ነገር የለም። ይህ ቢሆንም እንኳ “ህዝብ ባመነበት መንገድ መሪዎቹን በምርጫ እስኪመርጥ ድረስ”፤ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት የሚሆኑ ዕጩዎችን የማቅረብ ሂደት “የህዝብ ጥቆማ እና ተሳትፎ እንዲኖረው አስፈላጊ በመሆኑ” መላው የትግራይ ህዝብ በዚሁ ላይ እንዲሳተፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የክልሉ ህዝብ “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ስራዎች በብቃት ይፈጽማሉ፣ የክልሉን ሰላም እና ደህንነት ማረጋገጥ ይችላሉ” ያላቸውን ዕጩዎች ከዛሬ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የኤሜይል አድራሻ በኩል መጠቆም እንደሚችልም አብይ አሳስበዋል። የዕጩዎች ጥቆማ ጊዜ መቼ እንደሚያበቃ በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ላይ አልተገለጸም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)   

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]