የትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ማህበራት ህብረት አዲሱ የክልሉ የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፤ የፕሪቶሪያውን ግጭት በዘላቂነት የማቆም ስምምነት “መሰረት ያደረገ አይደለም” በማለት እርምት እንዲደረግ ጠየቀ። የትግራይ ልማት ማህበር ባለፈው ሳምንት ያደረገው ጉባኤ “ፖለቲካዊ ውግን እና ቅስቀሳ የታየበት ነው ያለው” ህብረቱ፤ ጉባኤው እንደገና እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል።
ሰባ ሁለት የሲቪል ማህበረሰብ ማህበራትን ያቀፈው ህብረቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አቋሙን ያሳወቀው፤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ሚያዝያ 22፤ 2017 ባወጣው መግለጫ ነው። ህብረቱ በዚሁ መግለጫው “በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ፖለቲካዊ ቀውስ ወደ ባሰ ሁኔታ ተሸጋግሮ አሸናፊ እና ተሸናፊ ወደ ሌለበት አደገኛ ሁኔታ ተገብቷል” ብሏል።
በክልሉ ላለው ፖለቲካዊ ችግር መፍትሔው፤ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት በማካሄድ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ እንዲፈታ ማድረግ እንደሆነ ህብረቱ አቋሙን ገልጿል። ለዚህም ሲባል ክልላዊ መድረክ እንዲጠራ እና ውይይት እንዲጀመር የማህበራት ህብረቱ ጥሪ አቅርቧል።

ህብረቱ በዚሁ መግለጫው በቅርቡ የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፤ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት “አቃፊ ሆኖ መመስርት ይገባው” እንደነበር ጠቅሷል። ሆኖም በሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው ካቢኔ፤ የፌደራል መንግስት በክልሎች ጣልቃ የመግባት አሰራርን ብቻ ተከትሎ የተመሰረተ እና “በጥቂት አካላት የሚመራ” በመሆኑ፤ አካሄዱ “ለቅቡልነት፣ አቃፊነት እና ውጤታማነት እንቅፋት ይሆናል” ሲል ህብረቱ አስገንዝቧል።
አዲሱ ካቢኔ የተዋቀረው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ምክር ቤት ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ እንደሆነ የገለጸው ህብረቱ፤ ይህ ደግሞ የክልሉን ፖለቲካዊ ቀውስ ይበልጥ የሚያባብስ እንደሆነ አመልክቷል። አሁን ስልጣኑን የተረከበው ጊዜያዊ አስተዳደር ላለፉት ሁለት ዓመታት በኃላፊነት ላይ የቆየውን አስተዳደር አሰራር ከገመገመ እና አዲሱን መዋቅር በተመለከተ ውይይት ካካሄደ በኋላ ካቢኔውን ሊመሰረት ይገባ እንደነበር ጠቁሟል።
“የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ጥቂት ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት እና አቃፊ ያልሆነ ነው” ያለው መግለጫው፤ የተቋቋመበት ሂደቱ እንዲታረም ጠይቋል። በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ አወቃቀር ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ ትችቶች መሰንዘራቸው ይታወሳል።
ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት (ዓረና)፣ ወድብ ናፅነት ትግራይ (ውናት) እና የብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) ባለፈው ሳምንት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ አዲሱ ካቢኔ “ለአንድ ቡድን ያደላ ነው” በማለት እንደማይቀበሉት ገልጸዋል። ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) ፓርቲም እንዲሁ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ ካቢኔው አቃፊ እና አሳታፊ አይደለም በማለት ዳግመኛ እንዲቋቋም ጠይቋል።
የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አስተዳደርም ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቋል። የትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ማህበራት ህብረት በረቡዕ መግለጫው፤ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የካቢኔ አወቃቀር በተጨማሪ የትግራይ ልማት ማህበርን ጉዳይ አንስቷል።
የትግራይ ልማት ማህበር የሲቪል ማህበረሰብ ማህበራት ህብረቱ አባል በመሆኑ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ጉባኤ ላይ የህብረቱ ተወካዮች መገኘታቸውን በመግለጫው ሰፍሯል። በጉባኤው “ፖለቲካዊ ውግንና እና ቅስቀሳ የታየበት” እንደነበር የገለጸው ህብረቱ፤ ይህ አካሄድ “የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን አዋጅን የሚጻረር ነው” ሲል ተችቷል።

በ2011 ዓ.ም የተሻሻለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ፤ የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅት “ከማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት ያልወገነ” መሆን እንዳለበት ይደነግጋል። በባለፈው ሳምንቱ የትግራይ ልማት ማህበር ጉባኤ የተመረጠው የድርጅቱ አዲስ ቦርድ፤ “በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሚመራው በብዛት የተያዘ ነው” በሚል ሲያወዛግብ ቆይቷል።
የትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ማህበራት ህብረት በረቡዕ መግለጫው፤ የትግራይ ልማት ማህበርን ለሚቀጥሉ ሶስት አመታት እንዲመሩ የተመረጡት የቦርድ አባላት እና አመራሮች “ተቀባይነት የላቸውም” ሲል ተቃውሟል። የልማት ማህበሩ ጉባኤ በተቋሙ ህገ ደንብ መሰረት እንደገና እንዲካሄድ እና አዲስ አመራሮች እንዲመረጡም ህብረቱ ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)