በቤርሳቤህ ገብረ
በአዲስ አበባ ከተማ በብስክሌት የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የስራ ፈቃድ የሚጠይቅ ሰው፤ 300 እና ከዚያ በላይ ብስክሌቶች ለአገልግሎት ማቅረብ የሚችል መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ደንብ ስራ ላይ ዋለ። ለአገልግሎት የሚቀርበው ብስክሌት ደረጃውን የጠበቀ ጂፔኤስ የተገጠለመት እና የተመረተበት ዘመን ከሁለት ዓመት ያልበለጠ መሆን አንዳለበትም አዲሱ ደንቡ ይደነግጋል።
“የብስክሌት መጋራት አገልግሎት እና የብስክሌት መስመር አጠቃቀም” የተሰኘ መጠሪያ ያለው ይህ ደንብ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የጸደቀው ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ነበር። ደንቡን ማዘጋጀት ካስፈለገባቸው ምክንያቶች አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ የተሽከርካሪ ቁጥር “በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ” ምክንያት የሚፈጠረውን “የትራፊክ እንቅስቃሴ መጨናነቅን ለማቃለል” እንደሆነ ተገልጿል።
ከቦታ ቦታ የሚደረግ እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ፣ የከባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ እንዲሁም የከተማይቱ ነዋሪዎች ብስክሌትን በማሽከርከር፣ የአካል ብቃታቸውን በማዳበር፣ ጤናማ ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል የሞተር አልባ ትራንስፖርት ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑም ተጠቅሷል። ለዚህም ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ወጭ ቆጣቢ፣ ተደራሽ፣ ፍትሃዊ፣ ዘላቂነት ያለው እና የማህበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት የአሰራር ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ደንቡን ማውጣቱ ተመልክቷል።

ደንቡ የብስክሌት የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ለሁለት ይከፍላቸዋል። የመጀመሪያው የትራንስፖርት አገልግሎት፤ ብስክሌቱን የሚያሽከረክረው ሰው በራሱ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስበት ነው። ሁለተኛው የአገልግሎት አይነት፤ ብስክሌቱ ባለው የእቃ መጫኛ ማስቀመጫ ቦታ በመጠቀም ዕቃዎችን እና መልዕክቶችን ማመላለስን የሚመለከት እንደሆነ በደንቡ ላይ ሰፍሯል።
በስድስት ክፍሎች እና በ25 አንቀጾች የተከፋፈለው ይህ ደንብ የስራ ፈቃድ አሰጣጥን ጨምሮ ሌሎች ድንጋጌዎችን አካትቷል። አዲሱ ደንብ ማንኛውም በብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት ለመሰማራት የሚፈልግ ሰው፤ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የስራ ፈቃድ ማውጣት እንዳለበት ይደነግጋል።
“በኦፕሬተርነት ስራ” ለመሰማራት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በመስፈርትነት ሊያሟላቸው የሚገባቸው መስፈርቶችም በደንቡ ላይ ተዘርዝረዋል። በዚህ ዘርፍ የስራ ፈቃድ ለማግኘት የሚፈልግ ሰው፤ የስራ ውል ስምምነት የሚፈርም እና ስራው የሚመራበት ቢሮ ያለው ሊሆን እንደሚገባ በመስፈርቱ ላይ ተቀምጧል።

ለኦፕሬተርነት ፈቃድ የሚያመለክት ግለሰብ፤ የብስክሌት ኦፕሬሽን እና የብስክሌት ጥገና ዘርፍ የስራ ክፍሎች ያሉት ሊሆን እንደሚገባ እና ለጥገና የሚሆኑ መሳሪያዎች ማሟላት እንደሚያስፈልገው በደንቡ ተደንግጓል። ኦፕሬተሩ በየብስክሌት ጣቢያው የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ መስጫ ኪት ማዘጋጀት የሚችል መሆንም ይኖርበታል።
በስራው የሚሰማራ ሰው ቢያንስ 300 እና ከዚያ በላይ ብስክሌቶች ወይም ከ100 የማያንስ ስኩተሮች ለአገልግሎት ማቅረብ የሚችል መሆን እንዳለበትም በደንቡ ላይ ሰፍሯል። ለአገልግሎት የሚቀርቡት ብስክሌቶች፤ ደረጃውን የጠበቀ ጂፒኤስ ያላቸው ወይም የተገጠመላቸው ሊሆን እንደሚገባ በመስፈርቱ ተካትቷል።
ማንኛውም ኦፕሬተር ለአገልግሎት የሚያቀርበው ብስክሌት የተመረተበት ዘመን ከሁለት አመት ያልበለጠ መሆን እንዳለበት ደንቡ ያዝዛል። በማንዋል፣ በኤሌክትሪክ ባትሪ ወይም በሀይብሪድ የሚሰሩ ብስክሌቶች አገልግሎት ለመስጠት ሊውሉ እንደሚችሉ ደንቡ ይፈቅዳል። ሆኖም በአንድ ኦፕሬተር የሚገኙ ብስክሌቶች ቀለም አንድ ወጥ ሆኖ ከሌላው ጋር የማይመሳሰል መሆን እንዳለበት ደንቡ ይስገድዳል።

ይህ ደንብ ካለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ እየተተገበረ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። በአሁኑ ወቅት የስራ ፈቃድ ለማግኘት ፕሮፖዛል ያስገቡ ግለሰቦች እንዳሉ የገለጸው ቢሮው፤ አመልካቾቹ በደንቡ የተቀመጡ ዝርዝር መስፈርቶችን እንዲያሟሉ በማድረግ ስራውን ለማስጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየተከናወኑ እንደሆነ እንደሚገኝ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)