በተስፋለም ወልደየስ
የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ መሬትን በሊዝ በባለቤትነት መያዝ የሚያስችላቸው የአዋጅ ረቂቅ፤ በነገው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊቀርብ ነው። ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው ግለሰቦች በኢትዮጵያ መሬትን፣ የመኖሪያ ቤትን ወይም ተያያዥ ግንባታዎችን በባለቤትነት ለመያዝ፤ ቢያንስ 150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሊመድቡ እንደሚገባ በአዲሱ አዋጅ ተደንግጓል።
የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት “ባለቤት” ወይም “ባለይዞታ” የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣውን ይህን አዋጅ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወያይቶ ለፓርላማ የመራው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር። አዋጁ የተዘጋጀው “የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት” ወይም “ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል መሬት የሚያገኙበትን” ህጋዊ አሰራር ለመዘርጋት እንደሆነ በመግቢያው ላይ ሰፍሯል።
“መኖሪያ ቤት” ማለት “ለግለሰብ ወይም ለቤተሰብ መኖሪያነት የሚያገለግል፤ ለንግድ ዓላማ ማዋል የማይፈቀድ ቤት” እንደሆነ በአዋጅ ረቂቁ የትርጓሜ ክፍል ላይ ተቀምጧል። ሆኖም ይህን መሰሉን ቤት “ለመኖሪያነት ዓላማ የማከራየት መብት የተጠበቀ” መሆኑን አዋጁ አመልክቷል።
በውጭ ዜጋ “በሊዝ ባለይዞታነት” ወይም “ባለቤትነት” የሚያዝ መሬት ወይም የመኖሪያ ቤት፤ “የማይንቀሳቀስ ንብረት” ተደርጎ እንደሚወሰድ የአዲሱ አዋጅ የትርጓሜ ክፍል ያብራራል። ይኸው ክፍል “ሊዝ”ን የሚተረጎመው “አግባብነት ባለው ህግ መሰረት በጊዜ በተገደበ ውል ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ዓላማ የሚውል የከተማ ወይም የገጠር መሬት የሚገኝበት የመሬት ይዞታ ስሪት” በሚል ነው።
ማንኛውም የውጭ ዜጋ በኢትዮጵያ “የማይንቀሳቀስ ንብረት” “ባለቤት” ወይም “ባለይዞታ” ሊሆን የሚችለው፤ በአዋጁ የተዘረዘሩ ቅደመ ሁኔታዎችን ሲያሟላ መሆኑም በህግ ረቂቁ ላይ ተደንግጓል። በቅደመ ሁኔታ ዝርዝሩ ላይ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የተቀመጠው፤ የውጭ ዜጋው “ስም፣ ዜግነት እና ሌሎችን ማንነትን የሚገልጹ ህጋዊ ሰነዶችን ማቅረብ” የሚለው መስፈርት ነው።
የውጭ ዜጋው የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለመብት ለመሆን የሚያስፈልግ “አነስተኛ የገንዘብ መጠን” ለማሟላት የሚያስችል “በቂ አቅም ያለው” መሆኑም በአዋጁ በቅድመ ሁኔታነት ተቀምጧል። ማንኛውም የውጭ ዜጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ለመሆን፤ “የሊዝ ዋጋውን ጨምሮ ለአንድ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሙሉ ዋጋ ወይም ለመኖሪያ ቤት ግዢ የሚመድበው” አነስተኛ የገንዘብ መጠን “ከ150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ሊሆን አይችልም” ይላል የአዋጅ ረቂቁ።
“ማንኛውም የውጭ ዜጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ለመሆን፤ የሊዝ ዋጋውን ጨምሮ ለአንድ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሙሉ ዋጋ ወይም ለመኖሪያ ቤት ግዢ የሚመድበው አነስተኛ የገንዘብ መጠን ከ150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ሊሆን አይችልም”
– የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ረቂቅ
ሌላው በቅድመ ሁኔታነት የተዘርዘረው፤ የውጭ ዜጋው “የወንጀል ሪከርድ የሌለበት” መሆን ይገባዋል የሚለው ነው። እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟላ አንድ የውጭ ዜጋ፤ ከከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሚሰጥ ፈቃድ ሊያገኝ እንደሚገባም በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተመልክቷል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “የፈቃድ ይሰጠኝ” ማመልከቻ ላቀረበ የውጭ ዜጋ፤ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ በ15 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል።
የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከዚህ በተጨማሪ ከውጭ ዜጎች የሚጠበቀውን የአነስተኛ ገንዘብ መጠን “ከፍ” ወይም “ዝቅ የሚያደርግ”፣ የእያንዳንዱን የሊዝ ቦታ ወይም ቤት “ስፋት” እንዲሁም የሊዝ ይዞታዎችን ወይም ቤቶችን “አጠቃላይ ቁጥር” የሚወስን መመሪያ የማውጣት ስልጣን በአዋጅ ረቂቁ ተሰጥቶታል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መመሪያውን የሚያወጣው፤ “የቤቶች ገበያ ወቅታዊ ሁኔታን፣ የከተሞች የማይንቀሳቀስ ንብረት አማካይ ዋጋን፣ የውጭ ዜጎች በቤቶች ገበያ ያላቸውን የተሳትፎ መጠን እና የአዋጁን ዓላማ ለማሳካት የሚረዱ ሌሎች ምክንያቶችን” መሰረት በማድረግ እንደሆነ የአዋጅ ረቂቁ ያስረዳል።
ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ፤ “የተወሰኑ ሀገራት ዜጎችን” ወይም “ዜግነት የሌላቸው” የውጭ ሀገር ሰዎችን በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ እንዳይሆኑ “ሊከልክል” እንደሚችል በአዲሱ አዋጅ ላይ ሰፍሯል። ለውጭ ዜጎች የተገደቡ “ልዩ ቦታዎች” እና “የድንበር አካባቢዎችም” እንዲሁ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናሉ” ሲል የአዋጅ ረቂቁ ያትታል።

አዲሱ አዋጅ ከቦታዎች እና አካባቢዎች በተጨማሪ በውጭ ዜጎች ላይ የተጣሉ ሌሎች ገደቦችንም አካትቷል። ማንኛውም የውጭ ዜጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ ለመሆን “ከሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋም ወይም ምንጭ” “ገንዘብ መበደር ወይም ካፒታል ማሰባሰብ” እንደማይችል አዋጁ ደንግጓል።
የውጭ ዜጎች ይህን ጉዳይ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ የሊዝ፣ የቤት ግዢ፣ የግንባታ ፈቃድ ወይም ተያያዥ የመንግስታዊ አገልግሎት ክፍያዎችን መክፈል ያለባቸው “በኢትዮጵያ ተቀባይነት ባለው የውጭ ምንዛሬ ብቻ” እንደሆነ የህግ ረቂቁ ግዴታ ያስቀምጣል። የአዋጅ ረቂቁ “ማንኛውም የውጭ ዜጋ በመንግስት ቀጥተኛ ድጎማ ለዜጎች በሚሰሩ የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች ውስጥ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት መሆን አይችልም” የሚል ክልከላም በውስጡ ይዟል።
ይህ ገደብ “በግል እና በመንግስት አጋርነት ወይም በተመሳሳይ የቤቶች ልማት ማዕቀፍ” በፌደራል ወይም በክልል መንግስታት የሚገነቡ መኖሪያ ቤቶችን “አያካትትም”። ለውጭ ዜጎች የተቀመጠው ገደብ፤ በእነዚህ አካላት አማካኝነት “ለትርፍ ዓላማ ተገንብተው” ለሽያጭ የሚቀርቡ ቤቶች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆንም በህግ ረቂቁ ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]