ኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ባለሙያዎች፤ በተራዘመ የብድር አቅርቦት ሶስተኛ ግምገማ ላይ ከስምምነት ደረሱ። ግምገማው በአይ ኤም ኤፍ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ሲጸድቅ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፉ ተቋም ከሚበደረው 3.4 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 260 ሚሊዮን ዶላር ይለቀቅለታል።
የአይ ኤም ኤፍ ቦርድ ግምገማውን ከማጽደቁ በፊት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከይፋዊ አበዳሪዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን ዛሬ አርብ ግንቦት 22፤ 2017 ይፋ ያደረጉት፤ ከሁለት ወር ገደማ በፊት ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የነበረውን የአይ ኤም ኤፍ የባለሙያዎች ቡድን የመሩት አልቫሮ ፒሪስ ናቸው።
መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፤ ለኢትዮጵያ መንግስት 3.4 ቢሊዮን ዶላር የሚያበድርበት መርሃ ግብር ተግባራዊ የሆነው ባለፈው ሐምሌ 2016 ዓ.ም ነበር። የብድር ስምምነቱ፤ በገበያ ወደሚወሰን የውጪ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት መሸጋገርን ጨምሮ አምስት ቁልፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጦችን ያካተተ ነው።
በዚህ ስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሬ ግብይት ከሐምሌ 22፤ 2016 ጀምሮ በባንኮች እና በደንበኞቻቸው እንዲወሰን ሲደረግ፤ አይ ኤም ኤፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለመንግስት ለቅቋል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ቦርድ፤ በስምምነቱ የተካተቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አተገባበር ላይ የተደረገውን የመጀመሪያ ግምገማ ያጸደቀው ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።
በዚህ ጊዜ አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ ከተፈቀደው ብድር ውስጥ 340.7 ሚሊዮን ዶላር ያህሉን ለቅቋል። የኢትዮጵያ መንግስት ተጨማሪ 248 ቢሊዮን ዶላር ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የወሰደው፤ የአይ ኤም ኤፍ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ሁለተኛውን ግምገማ በጥር ወር መጀመሪያ በተመሳሳይ መልኩ ካጸደቀ በኋላ ነበር።
የተራዘመ የብድር አቅርቦት ሶስተኛው ግምገማ በድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ከጸደቀ፤ ከአጠቃላይ ብድሩ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው የገንዘብ መጠን 1.848 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይደርሳል። ለሶስተኛው ግምገማ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የነበረውን የአይ ኤም ኤፍ የባለሙያዎች ቡድን የመሩት አልቫሮ ፒሪስ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በመርሃ ግብሩ የመጀመሪያ ዓመት የወሰዷቸው የፖሊሲ እርምጃዎች “ጠንካራ ውጤቶች” ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

የሀገሪቱን የገንዘብ ፖሊሲ ለማዘመን፣ የሀገር ውስጥ ገቢ ለማሰባሰብ፣ የማህበራዊ ጥበቃ መርሃ ግብሮችን ለማጎልበት፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለማጠናከር እና ለፋይናንስ መረጋጋት መሰረት ለመጣል የተወሰዱ እርምጃዎች “አበረታች ውጤት ማሳየት መቀጠላቸውንም” አስታውቀዋል። አልቫሮ ፒሪስ የጠቀሷቸው አንኳር ጉዳዮች በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሃ ግብር ውስጥ የተካተቱ የኢትዮጵያ መንግስት የቤት ስራዎች ናቸው።
ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዝያ 9፤ 2017 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ የሰነበተው የአይ ኤም ኤፍ የባለሙያዎች ቡድን፤ በቆይታው ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ከምክትላቸው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ፣ ከብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ እና ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ውይይት አድርጓል። ቡድኑ ከዚህም በተጨማሪ ከባንኮች፣ ከንግዱ ማህበረሰብ እና ከሲቪል ማህበራት ተወካዮች ጋር መወያየቱን ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]






























