የእነ አቶ ጌታቸው ረዳ ፓርቲ በአንድ ወር ከአጋማሽ ውስጥ “በትግራይ መስራች ጉባኤዬን አካሄዳለሁ” አለ 

በተስፋለም ወልደየስ

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ ፍቃድ ያገኘው ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ (ስምረት)፤ እስከ አንድ ወር ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ መስራች ጉባኤውን እንደሚያካሄድ ገለጸ። ፓርቲው ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የአባላት ምልመላ እና ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ አደረጃጀቶችን የመፍጠር ስራዎችን እንደሚያከናውን አስታውቋል። 

ስምረት ፓርቲ ይህን የገለጸው፤ ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 23፤ 2017 በአዲስ አበባው ሸራተን ሆቴል በሰጠው የመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ጋዜጣዊ መግለጫውን ከፓርቲው መስራቾች አንዱ የሆኑት የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ይሰጡታል ተብሎ ቢጠበቅም፤ ባጋጠማቸው “የጤና እክል” ምክንያት በመግለጫው ሳይሳተፉ ቀርተዋል።

እርሳቸውን በመተካት መግለጫውን የሰጡት የአዲሱ ፓርቲ የሚዲያ እና የኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም፤ ፓርቲው በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥ ሁለት መሰረታዊ ስራዎችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል። መቶ አባላትን በመያዝ ጊዜያዊ ፍቃዱን ከምርጫ ቦርድ ያገኘው ስምረት፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከትግራይ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች አባላትን የመልመል ስራዎች እንደሚሰራ አቶ ረዳኢ ተናግረዋል።

“የፓርቲ ምልመላው በመሰረቱ ከሶስት አካላት ነው ዋናው ትኩረት የሚያደርገው። ሁሉም የህብረተሰብ አካል የሚያሳትፍ ቢሆንም አሁን መሰረታዊ ትኩረት የሚያደርግባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ግን ሶስት [ናቸው]። አንደኛው፤ የእኛ አባል የነበረ እና የለውጥ ኃይል የደገፈው [ነው]። ከአሁን በፊት የህወሓት አባል ሆኖ ግን ደግሞ ከደረቀው ሳይሆን ከለውጥ ኃይሉ ጋር ሆኖ እየታገለ ያለው አባልም፣ ካድሬም እንዳለ የሚቀጥል ይሆናል” ብለዋል አስተባባሪው።

አዲሱ ስምረት ፓርቲ፤ የህወሓት አባል ያልነበሩ ወጣቶችን እና ምሁራን ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም አቶ ረዳኢ ገልጸዋል። “በድምር እነዚህ የአዲሱ ትውልድ ክፍል ስለሚሆኑ፤ አዲሱ ትውልድ በስፋት የሚሳተፍበት፣ የነገውን ትግራይን ለመገንባት ልዩ አስተዋጽኦ እና ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርግበት እንዲሆን አስበን የምልመላ ስራችንን እንቀጥላለን” ሲሉም አብራርተዋል።

በ2012 ዓ.ም የወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ፤ የክልል የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት የአራት ሺህ መስራች አባላት ፊርማ ማሰባሰብን በግዴታነት ያስቀምጣል። ከአዲሱ ክልላዊ ፓርቲ መስራች አባላት ውስጥ “ከስልሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት” የክልሉ መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንዳለባቸው በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

“ከትግራይ ውጭ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያለ ትግራዋይም ቢሆን የሚመዘገብበትን ስርዓት እንፈጥራለን። በአዲስ አበባም፣ ከአዲስ አበባ ውጭ ያለውም ትግራዋይ፤ የስምረት ፓርቲ አባል ለመሆን የሚያበቃውን ነገር፣ ፕሮግራሙን ከተቀበለ አባል ይሆናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በትግራይ ውስጥ [ብቻ] ሳይሆን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እና በከተሞችም እንዲሁ አደረጃጀቶች ይኖሩናል” ሲሉ አቶ ረዳኢ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስረድተዋል። 

አዲሱ ፓርቲ በዳያስፖራ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን የሚያቅፉ አደረጃጀቶች በየአካባቢው እንደሚኖሩትም ተናግረዋል። የፓርቲውን አደረጃጀቶች በየደረጃው የማዋቀሩ ስራ በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱንም አመልክተዋል። ይህን ለማድረግ በትግራይ ውስጥ “ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ የተለያዩ መድረኮች ይኖሩናል” ብለዋል አስተባባሪው።

“እነዚህ መድረኮች ከተጠናከሩ፣ የአባል ምልመላው ከተጠናቀቀ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትግራይ ውስጥ ጉባኤ የምናካሄድ ይሆናል። ጉባኤው ክረምት ከማለቁ በፊት የሚጠናቀቅ ይሆናል። ምናልባት ከአንድ ወር እስከ አንድ ወር ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ መስራች ጉባኤ ይካሄዳል” ሲሉም አዲሱ ፓርቲ በመጪዎቹ ጊዜያት የሚያከናውናቸውን ተግባራት ዘርዝረዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለስምረት ፓርቲ የሰጠው ጊዜያዊ ፍቃድ የሚያገለግለው ለሶስት ወራት ብቻ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]