ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ብቻ ሲካሄድ የቆየው የባንክ ስራ አገልግሎት፤ ከዛሬ ጀምሮ ለውጪ ባንኮች እና ኢንቨስተሮች በይፋ መከፈቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ። በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ የውጪ ባንኮች እና ኢንቨስተሮች ከዛሬ ጀምሮ ማመልከቻዎቻቸውን ለብሔራዊ ባንክ ማስገባት እንደሚችሉም መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
አቶ ማሞ ምህረቱ በገዢነት የሚመሩት ብሔራዊ ባንክ ይህን ያስታወቀው፤ የውጭ ባለሃብቶች የባንክ ስራ ፈቃድ ለማግኘት እና ለማሳደስ የሚያስችላቸውን መመሪያ ይፋ ባደረገበት መግለጫ ነው። አዲሱ መመሪያ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የውክልና ጽህፈት ቤት ለመክፈት ማሟላት የሚያስፈልጋቸውን ቅድመ-ሁኔታዎችም ይዘረዝራል።
መመሪያው ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ዓመት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያደረገው “ሰፊ ምክክር” ውጤት እንደሆነ የመስሪያ ቤቱ መግለጫ አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ለውጪ ባንኮች እና ለኢንቨስተሮች ተዘግቶ የቆየውን የባንክ ስራ ዘርፍ ለመክፈት ዝግጅት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ወደ ተግባር የገባው ከሶስት ዓመት በፊት ነበር።

የኢትዮጵያ የባንክ ስራ ለውጪ ኢንቨስተሮች ክፍት እንዲሆን የሚፈቅድ ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው በነሐሴ 2014 ዓ.ም. ነበር። ፖሊሲውን ተግባራዊ የሚያደርገው የባንክ ስራ አዋጅ በፓርላማ የጸደቀው ደግሞ በዚህ ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ነው።
ብሔራዊ ባንክ በዛሬው መግለጫው፤ የባንክ ስራ ዘርፍ ለውጭ ባለሃብቶች መከፈት “ከፍተኛ ካፒታል እና ውድድር ያመጣል” የሚል ተስፋውን አንጸባርቋል። የዘርፉ መከፈት “የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ቅልጥፍና እና አካታችነትን ለማጠናከር ያግዛል” ሲልም ባንኩ በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
ከመንፈቅ በፊት በጸደቀው የባንክ ስራ አዋጅ መሰረት፤ የውጭ ኢንቨስተሮች ወይም የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ስራ ዘርፍ ውስጥ የሚሳተፉት በአራት አይነት መንገድ ነው። አዋጁ የውጪ ባንኮች በኢትዮጵያ ህግ መሰረት የሚቋቋም ተቀጥላ እንዲመሰርቱ አሊያም ቅርንጫፍ ከፍተው እንዲሰሩ ፈቅዶላቸዋል።
የውጪ ሀገር ባንኮች ወይም ኢንቨስተሮች፤ ከኢትዮጵያ ባንኮች የአክሲዮን ድርሻ መግዛት እንዲችሉም በዚሁ አዋጅ መሰረት ፈቃድ አግኝተዋል። በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ሌላኛው በአዋጅ የተቀመጠው መንገድ የእንደራሴ ቢሮ መክፈት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























