የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ህወሓት ከፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት በኋላ አድርጓቸዋል ያሏቸው “ትንኮሳዎች”፣ “እምቢ ባይነቶች”፣ “ስራዎች” እና “ሴራዎች”፤ “ወደ ጦርነት ለመግባት ከበቂ በላይ ናቸው” አሉ። ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ “ጉጅሌ” ሲሉ የጠሩት በህወሓት ውስጥ ያለ ኃይል “እስካልተነቀለ ድረስ ኢትዮጵያ ሰላም አታገኝም” ሲሉም ተደምጠዋል።
ኤታማዦር ሹሙ ይህን ያሉት፤ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት የተፈጸመበት አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። ትላንት ሰኞ ጥቅምት 24፤ 2018 በቢሾፍቱ አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል በተካሄደው በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰን ጨምሮ ከፍተኛ የጦር አዛዦች እና መኮንኖች ተገኝተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ከትላንቱ ንግግራቸው አብዛኛውን ቦታ የወሰደው፤ የሰሜን ዕዝ ጥቃት እንዴት እና በእነማን እንደተፈጸመ ያብራሩበት ነው። “የዛሬ አምስት ዓመት የተፈጸመውን ጥቃት “ክህደት” እና “አስነዋሪ ታሪክ” ሲሉ የጠሩት ኤታማዦር ሹሙ፤ ስለ ድርጊቱ ሲነሳ እየተወራ ያለው ስለ ህወሓት እንጂ ስለ ትግራይ ህዝብ አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ህወሓት ራሱም በሙሉ አይደለም። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ጅምላ ይሆኑና ሀገር የሚጎዳ ድምዳሜ ላይ ይደረሳል” ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ድርጊቱ “መካድ በለመደ” የተወሰነ የህወሓት ስብስብ (ጉጅሌ) የተፈጸመ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል። ስብስቡ እነማንን እንዳካተተ ኤታማዦር ሹሙ በንግግራቸው በግልጽ ባያመለክቱም፤ ይህን መሰል ስራውን ከጀመረ “50 ዓመት” እንደሆነው በመጠቆም የህወሓት የምስረታ ጊዜን አጣቅሰዋል።
“ግብጾች ሻዕቢያን ቀጥረው፣ ሻዕቢያ እሱን ቀጥሮ፣ ኢትዮጵያን ወግቶ ባህር በር ያሳጣን እና ሀገር ያስገነጠለ ከሃዲ ነው። ‘ኑ እንታረቅ’ ብሎ የፖለቲካ ድርጅቶችን በእርቅ መድረክ ጋብዞ፤ በሬ አርዶ፣ ያረደ ከሃዲ ነው። ሰሜን ዕዝ ላይም የደገመው እሱ ነው። አሁንም በየቀኑ ይክዳል” ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በትላንቱ ንግግራቸው ወንጅለዋል።
ኤታማዦር ሹሙ የተለያዩ ውንጀላዎች ያቀረቡበትን የህወሓት ስብስብ በተደጋጋሚ “በከሃዲነት” ሲፈርጁም ተደምጠዋል። “ይሄ ኃይል የሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረ የክህደት መንፈስ፣ የክህደት ኃይል ነው። ይሄ ኃይል እስካልተነቀለ ድረስ ኢትዮጵያ ሰላም አታገኝም” ሲሉም መጪውን ጊዜ ያመላከተ ንግግር አድርገዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ህወሓት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ፈጽሟቸዋል ያሏቸው “ትንኮሳዎች” እና “እምቢ ባይነቶች”፤ ዳግም ወደ ጦርነት ለመግባት “ከበቂ በላይ” እንደነበሩ ጠቁመዋል። ህወሓት “ተፈናቃይ አልለቅም” ማለቱን፣ “ኃይል ማሰልጠኑን”፣ ትጥቅ በማስፈታት እና በማቋቋም ሂደት (DDR) የተሰናበቱ ወታደሮችን “እንዲመለሱ” ማድረጉን ኤታማዦር ሹሙ ለዚህ አባባላቸው በማሳያነት ጠቅሰዋል።
“ጦረኛ መንግስት ቢሆን ኖሮ፣ ጦርነት የሚናፍቅ ቢሆን ኖሮ፣ ጦረኛ የመከላከያ ሰራዊት ቢሆን ኖሮ፤ ከፕሪቶሪያ በኋላ ህወሓት የሰራቸው ትንኮሳዎች፣ ስራዎች፣ ሴራዎች በቂ ናቸው – ወደ ጦርነት ለመግባት። ግን በጦርነት ህወሓት ይሸሻል። የትግራይ ህዝብ ይጎዳል። ባለፈው ጦርነት ያየነው እሱን ነው” ብለዋል ኤታማዦር ሹሙ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ህወሓት ከሻዕቢያ ጋር “ጽምዶ” በሚል ስያሜ ፈጥሮታል ያሉትን ህብረትም ወደ ጦርነት ሊያስገቡ ከሚችሉ ምክንያቶች ዝርዝር ውስጥ አካትተውታል። “ድንበር ሰብሮ መሄድ ጸረ- ህገ መንግስት ነው” ያሉት ኤታማዦር ሹሙ፤ ህብረት መፍጠሩ በራሱ “ክህደት ነው” ሲሉ አካሄዱን ነቅፈዋል።

“ ‘ጄኖሳይድ ፈጸመብኝ’ ስትል ከርመህ እንደገና ‘ሻዕቢያ ወዳጃችን ነው፣ አሊያንሳችን ነው፣ ከእኛ ጋር ይቁም፣ አብረን እንሰራለን፣ ኢትዮጵያን እንከዳለን፣ ኢትዮጵያን አብረን እንዳክማለን’ የሚል ነገር እየተካሄደ ነው። [ይሄ] በሌላ መልክ የሚገለጽ ክህደት ነው” ሲሉ ከፍተኛ የጦር አዛዡ ተናግረዋል።
ህወሓት ለፋኖ “ጥይት እና እቅድ ሰጥቶ”፤ ኢትዮጵያን እና አማራ ክልል “እንዲበጠበጥ” መላኩን በማንሳት የወነጀሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ይህ ድርጊት ወደ ጦርነት ሊያስገቡ የሚችል ሌላኛው ምክንያት እንደነበር አስረድተዋል። “በቀደም በሰሜን ወሎ ግንባር ከፋኖ ጋር ተገናኝታችሁ፣ ገብታችሁ፣ እቅድ አውጥታችሁ፣ አመራር እየሰጣችሁ፣ ተዋግታችኋል። ግን ዝም ብለናችኋል። ምክንያቱም ኃላፊነት አለብን። እኛ መንግስት ነን። ለትንኮሳ ሁሉ መልስ አንሰጥም። ሞልቶ ከፈሰሰ ግን ምንም ማድረግ አንችልም” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
“ይሄን ሁሉ እያየን ነው ዳግም ወደ ጦርነት ያልገባነው” ያሉት ኤታማዦር ሹሙ፤ “የአሁኑ እየሰሩ ያሉት ነገር ጉዳት አለው ግን ጦርነት ሲመጣ ደግሞ የበለጠ ጉዳት ያመጣል” በሚል ጊዜ ለመስጠት መወሰኑን አብራርተዋል። “በጊዜ ሂደት ብዙ ቀልብ የሚገዛ ሰው ይፈጥርና ይሄ ቀልብ የሌለው ሰው ተንገዋሎ ይቀራል’ በሚል ነው እየሄድን ያለነው” ሲሉም አክለዋል።
“ምንም ብንታገስ፣ ከተጠቃን፣ እንደ ዳግማዊ ሰሜን ዕዝ ከሆነ፣ መከላከላችን አይቀርም። ጦርነት እኛ ብቻ ማስቀረት አንችልም”
– ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፤ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በቴሌቪዥን በተላለፈው 40 ደቂቃ ንግግራቸው እርሳቸው የሚመሩት የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ውጊያ መግባት እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ ቢገልጹም፤ ጦርነት ሊቀሰቅስ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ግን ፍንጭ ሰጥተዋል። “ወንጀለኛ” ሲሉ የከሰሱት የህወሓት ስብስብ፤ “የትግራይን ህዝብ ዕጣ ፈንታ መወሰን የለበትም” ሲሉም አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል።
“ምንም ብንታገስ፣ ከተጠቃን፣ እንደ ዳግማዊ ሰሜን ዕዝ ከሆነ፣ መከላከላችን አይቀርም። ጦርነት እኛ ብቻ ማስቀረት አንችልም” ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ “አንቸኩልም፣ ጦርነት አንቀሰቅስም፣ ጦርነት አንፈልግም። በሰላማችን ላይ፣ በብሔራዊ ጥቅማችን ላይ የመወጣውን ግን፣ ከድንበር ያለፈ ግን መዋጋት አለብን። የተደራጀነውም፣ የታጠቅነውም ለዚያ ነው” ሲሉ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ጠንከር ያሉ ገለጻዎች የሞሉበት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ንግግር የተደመጠው፤ የአውሮፓ ህብረት፣ የህብረቱ አባል ሀገራት እና ኖርዌይ በፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚዎች መካከል “ፖለቲካዊ ውይይት” “እንደገና እንዲቀጥል” ጥሪ ባቀረቡ ማግስት ነው። የዛሬ ሶስት ዓመት ጥቅምት 23፤ 2015 በደቡብ አፍሪካዋ የፕሪቶሪያ ከተማ የግጭት ማቆም ስምምነት የፈረሙት የፌደራል መንግስት እና የህወሓት ተወካዮች ነበሩ።
ስምምነቱ የተፈረመበትን ሶስተኛ ዓመት በማስመልከት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተልዕኮ፣ 22 የህብረቱ አባል ሀገራት እና ኖሮዌይ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ የፖለቲካዊ ውይይቱ ከመጪው ምርጫ በፊት መልሶ መጀመር እንዳለበት አሳስበዋል። ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስን ጨምሮ ከግጭት ማቆም ስምምነቱ ጋር የተያያዙ ሂደቶችን ለመደገፍም ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























