በኢትዮጵያ “የሀሳብ ትግል” ለሚያደርጉ ሁሉ በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት “ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ። ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያሉ ተቋማትን እንዲመሩ የተሾሙ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፤ በሚያከናውኗቸው ስራዎች እና ውሳኔዎቻቸው ላይ “ማንም ጣልቃ እንዳይገባባቸው አድርገናል” ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ካሉት ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶች አንዱ የሆኑት አቶ አደም ይህን ያሉት፤ ለገዢው ፓርቲው ቅርበት ካለው ፋና የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ነው። ትላንት ሰኞ ታህሳስ 13፤ 2018 በተላለፈው በዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ “ሀሳብ አልባ ፖለቲካ” እና የመጪው ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ይገኙበታል።
በኢትዮጵያ “በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ ስርዓት” የበላይነት እንዲይዝ “የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት” እና “ጤናማ ማድረግ” አስፈላጊ መሆኑን በቃለ ምልልሳቸው ላይ የጠቀሱት አቶ አደም፤ ከዚህ አኳያ ባለፉት ዓመታት በተሰራው “ሪፎርም” ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል። በሀገሪቱ ውስጥ “አማራጭ ሃሳብ አለኝ” የሚል አካል፤ “በሙሉ በነጻነት መንቀሳቀስ እንዲችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል” ሲሉም ተደምጠዋል።

“በአሁኑ ወቅት ‘ሃሳብ አለኝ፣ የራሴን ፓርቲ መስርቼ መታገል እፈልጋለሁ’ የሚል አካል ላይ እንቅፋት የሚፈጥር አካል የለም። ያሉትም በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ነው ጥረት የሚደረገው። ችግር እንኳ ቢኖር ደግሞ ችግሩን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉ አቶ አደም አክለዋል።
የገዢውን ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት በኃላፊነት የሚመሩት አቶ አደም ይህን ቢሉም፤ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና አግኝተው የፖለቲካ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉባኤዎቻቸውን ጨምሮ መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንዳልቻሉ ባለፉት ዓመታት ወቀሳ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ለማካሄድ አቅዶት የነበረው ህዝባዊ ስብሰባ በገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ ምክንያት መሰረዙ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።
ኢህአፓ “አዲስ አበባ ትናገራለች” በሚል መሪ ሀሳብ ለማካሄድ ላቀደው ህዝባዊ ስብሰባ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ፈቃድ አግኝቶ እንደነበር ጉዳዩን በተመለከተ ህዳር 26፤ 2018 ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። “ስርዓቱ በማይታየው እጁ ከጀርባ ሆኖ” የአዲስ አበባው ህዝባዊ ስብሰባ እንዳይካሄድ “መከልከሉን” እንደሚረዳ በመግለጫው ላይ የጠቀሰው ኢህአፓ፤ በዚህም ምክንያት ውይይቱን ለመሰረዝ መገደዱን አስታውቋል።

የገዢው ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት በትላንትናው ዕለት በተላለፈ ቃለ ምልልሳቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ አካባቢዎች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች “ችግር ተፈጥሮብናል” ሲሉ ይህንኑ የሚፈቱባቸው መድረኮች መመቻቸታቸውን አንስተዋል። በየደረጃው የተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ “ችግር ሲገጥም እዚያው መፍትሔ እንዲሰጡ” እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
“ [የፖለቲካ ፓርቲዎች] ቅሬታቸውን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በኩል ይሁን በሌሎች መንገድ ሲያቀርቡ፤ እኛ እንደ ገዢ ፓርቲ ትኩረት ሰጥተን፣ ለዚያ የሚመጥን አመራር መድበን፣ ችግሩ እንዲፈታ ለማድረግ ነው [የምንጥረው]” ሲሉ አቶ አደም የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያሰሟቸውን ክሶች ተከላክለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተመለከተ በቃለ ምልልሳቸው የጠቀሱት ሌላው ጉዳይ፤ በገዢው ፓርቲ ተደጋግሞ የሚነሳው “የስልጣን ማጋራትን” አካሄድ ነው። በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት መመስረት የሚያስችላቸውን ድምጽ ባያገኙም፤ “ኃላፊነቶችን እንዲለማመዱ” በሚል በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተመድበው እየሰሩ እንደሆነ አቶ አደም አስታውሰዋል።
በዚህም መሰረት ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ “275 የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት” ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያሉ ተቋማትን እንዲመሩ መደረጉን አቶ አደም ገልጸዋል። በእነዚህ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የዕለት ተዕለት የአመራር ስራዎቻቸው እና ውሳኔዎቻቸው ላይ “ማንም ጣልቃ እንዳይገባባቸው አድርገናል” ሲሉም ተደምጠዋል።
ገዢው ፓርቲ ስልጣን ካጋራቸው ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ፤ ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ሃሳብ አንጸባርቆ ነበር። ፓርቲው በፌደራል፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በሌሎች ክልሎች ባገኘው የኃላፊነት ቦታ፤ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሲሰራ መቆየቱን በዚሁ መግለጫ ላይ ተነግሯል።
መግለጫውን ከሰጡት አመራሮች አንዱ የኢዜማ የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኢዮብ መሣፍንት፤ የፓርቲያቸው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በትምህርት ሚኒስትርነት ኃላፊነታቸው ያለማንም ጣልቃ ገብነት “ያመኑበትን ሲሰሩ” መቆየታቸውን ገልጸዋል። አቶ ኢዮብ በትምህርት ሚኒስቴር “የምንኮራበትና ለቀጣዩ ምርጫ ቅስቀሳ የምንጠቀምበትን ሥራ ሰርተናል” ማለታቸው መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
ኢዜማ ይህን ቢልም ከገዢው ፓርቲ ጋራ የመንግሥት ሥልጣንን የተጋሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ “የብልጽግና ፓርቲ አቋም አራማጆች ናቸው” የሚል ትችት ከተለያዩ አካላት ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል። ከኢዜማ ለቅቀው የወጡ የቀድሞ አመራሮች፤ ፓርቲው የብልጽግናን የሹመት ጥያቄ ለመቀበል መስማማቱን ለውሳኔያቸው በዋና ምክንያትነት መጥቀሳቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































