“ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ” የተሰኘ ድርጅት፤ ዓለም-አቀፋዊ እና ሕገ-መንግስታዊ “ግዴታቸውን እና ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት” “በተፈናቃዮች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲደርሱ አድርገዋል” ያላቸውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የሰላም ሚኒስቴር እና ሶስት ክልሎችን በፍርድ ቤት ከሰሰ። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመመልከት ለነገ አርብ ለታኀሣሥ 17፤ 2018 ቀጠሮ ሰጥቷል።
ሀገር በቀል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የክስ ማመልከቻውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ችሎት ያስገባው ባለፈው ጥቅምት 25፤ 2018 ነው። በዳኞች በተሰጠ ትዕዛዝ መሰረት የክስ መዝገቡ እንዲከፈት የተደረገው ህዳር 5 ቢሆንም፤ ችሎቱ የክስ መዝገቡን ለመመልከት ቀጠሮ የሰጠው ለታኀሣሥ 10 ነበር። ሆኖም በዕለቱ ዳኞቹ ባለመሟላታቸው ምክንያት ችሎቱ መዝገቡን ለመመልከት የሰጠውን ቀጠሮ በአንድ ሳምንት አራዝሟል።
ድርጅቱ ክሱን ያቀረበው በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ለተፈናቀሉ “የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ዜጎች ጥቅም” መሆኑን በክስ ማመልከቻው ላይ ገልጿል። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ከአፋር፣ ትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ላይ “ደርሷል” ያለውን “የሰብአዊ መብት ጥሰት” በክስ ማመልከቻው በዝርዝር አስፍሯል።

የየትኞቹ ተፈናቃዮች ጉዳይ በክሱ ተካትቷል?
ድርጅቱ በክሱ በመጀመሪያ ላይ የጠቀሰው፤ ህዳር 24፤ 2013 በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ከትግራይ ምዕራባዊ ዞን እና ከአፋር ክልል ሸኸት ወረዳ የተፈናቀሉ ሰዎችን ጉዳይ ነው። በዚሁ ጦርነት “ከአንድ ሚሊዮን 57 ሺህ በላይ” የትግራይ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ድርጅቱ አመልክቷል።
ወደ ቀዬአቸው ያልተመለሱት እነዚህ ተፈናቃዮች፤ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ እና ከማኅበረሰቡ ጋራ እየኖሩ እንደሆነ ድርጅቱ በክሱ ላይ ጠቁሟል። በተመሳሳይ ሁኔታ ከኦሮሚያ ክልል “በግጭት እና በተለያዩ ምክንያቶች” የተፈናቀሉ “ከ519 ሺህ በላይ ዜጎች”፤ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ድርጅቱ ጠቅሷል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የክስ ማመልከቻ፤ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ “ከ84 ሺህ በላይ ዜጎች” እንዳሉ ይገልጻል። እነዚህ ተፈናቃዮች በትግራይ ክልል እንዳሉት ሁሉ፤ በጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው ወይም ከማኅበረሰቡ ተጠግተው እንደሚገኙ ድርጅቱ የክስ ማመልከቻው ያስረዳል።
በሶስቱም ክልሎች ያሉ ተፈናቃዮች በተጨናነቁ መጠለያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና “ክፍት ቦታዎች” ጭምር እንደተጠለሉ የጠቀሰው የድርጅቱ ማመልከቻ፤ ውሃ፣ መጸዳጃ፣ ምግብ እና የጤና አገልግሎት በቂ በሆነ መልኩ እያገኙ እንዳልሆነ አትቷል። ተፈናቃዮቹ “እጅግ አስከፊ” ሲል ድርጅቱ በጠራው የደህንነት እና የሞራል ውድቀት ውስጥ እንዳሉ በክሱ ላይ የገለጸው ድርጅቱ፤ በረሃብ የተጠቁ እንዳሉም አስታውቋል።

በተከሳሾቹ ላይ የቀረበው የክስ ዝርዝር ምንድነው?
“ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ” የተሰኘው ድርጅት ለፍርድ ቤት ባቀረበው ማመልከቻ ላይ የዘረዘራቸው ተከሳሾች አምስት ናቸው። በተከሳሾች ዝርዝር በአንደኛ ተራ ቁጥር የተቀመጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲሆን እርሱን ተከትሎ በሁለተኛነት የሰፈረው የሰላም ሚኒስቴር ነው።
የአማራ ክልላዊ መንግሥት፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፤ በድርጅቱ የክስ ማመልከቻ ላይ ከሶስት እስከ አምስተኛ ያሉትን የተከሳሽነት ቦታዎች ይዘዋል። ድርጅቱ በማመልከቻው ላይ ሁሉም ተከሳሾች የተፈናቃዮችን ሕገ-መንግስታዊ እና ዓለም-አቀፋዊ መብቶች “እየጣሱ ይገኛሉ” ሲል ወንጅሏል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ፤ ተፈናቃዮቹ በሕገ-መንግስቱ የተሰጣቸው “የአካል ደህንነት”፣ “በሕይወት የመኖር”፣ “የመንቀሳቀስ” እና “በፈለጉት የኢትዮጵያ ግዛት የመኖር” እንዲሁም “በቂ የመንግሥት ድጋፍ የማግኘት” መብቶች እንዳሏቸው በክስ ማመልከቻው ላይ ዘርዝሯል። ተፈናቃዮቹ እነዚህ ሕገ መንግስታዊ መብቶች “እንደተጣሱባቸው” ድርጅቱ በክሱ ላይ አመልክቷል።

ከሕገ መንግስቱ በተጨማሪ ሁሉም ተከሳሾች በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን መጠበቅ እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ የሚያስገድደውን የአፍሪካ ህብረት የካምፓላ ኮንቬንሽን በመጣስ ክስ ቀርቦባቸዋል። ይህንን የካምፓላ ኮንቬንሽን ኢትዮጵያ በየካቲት 2012 ዓ.ም ተቀብላ ያጸደቀች ሲሆን፤ ከአንድ ወር በኋላም በአዋጅ መልክ ተዘጋጅቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ አድርጋለች።
የካምፓላ ኮንቬንሽን፤ በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን “ወደ ቀዬአቸው የመመለስ”፣ “በቂ የጸጥታና ደህንነት ሽፋን የመስጠት” እና “በቂ የማቋቋሚያ እርዳታ የማቅረብ” ግዴታ በፈራሚ ሀገራት ላይ ይጥላል። ከሃምሳ አምስቱ የአፍሪካ ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ኮንቬንሽኑን ተቀብለው ያጸደቁ ሀገራት 34 ብቻ ናቸው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የሰላም ሚኒስቴር እነዚህን ሕጎች “የማስፈጸም” እና “የመከታተል” ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል በድርጅቱ ተከስሰዋል። በምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች ይኖሩ የነበረበትን ቀዬ “በመያዝ” እና “በማስተዳደር” “እንዳይመለሱ በመከልከል” ክስ የቀረበበት ደግሞ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ነው።

የክልሉ መንግስት ይህን ድርጊት በመፈጸሙ፤ ተፈናቃዮቹ “በከፍተኛ ስቃይ እና ሰቆቃ ውስጥ ለዓመታት እንዲቀጥሉ ሆኗል” ሲል “ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ” በክስ ሰነዱ ላይ አመልክቷል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም ከእነዚሁ ተፈናቃዮች ጋር በተገናኘ ተከስሷል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶሪያ ስምምነትን መሰረት በማድረግ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ከሰላም ሚኒስቴር ጋር “ንግግር” እና “ጥረት በማድረግ” ተፈናቃዮቹ እንዲመለሱ መስራት ይገባው እንደነበር በክስ ማመልከቻው ላይ ሰፍሯል። ሆኖም ጊዜያዊ አስተዳደሩ “የራሱን ፖለቲካዊ ጉዳይ በማስቀደም” “ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ” በክሱ ላይ ተወንጅሏል።
በአምስተኛ ተከሳሽነት የተጠቀሰው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተከሰሰው፤ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠበት የሀገሪቱ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው” የሚደነግገውን የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 32 “ጥሷል” በሚል ነው። የክልሉ መንግሥት፤ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ማመቻቸት ሲገባው “ኃላፊነቱን አለመወጣቱን” በክሱ ላይ ተመልክቷል።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ በክሱ ማሳካት የፈለገው ምንድነው?
“ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ”፤ ክሱን ከሚመለከተው ፍርድ ቤት የተፈናቃዮችን መብት የሚያስጠብቅ ውሳኔ እንደሚጠብቅ አስታውቋል። በዚህም መሰረት ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ ተፈናቃዮች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የአማራ እና የትግራይ ክልል መንግስታት “ተገቢውን ተግባራዊ እርምጃ” እንዲወስዱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ድርጅቱ በክስ ማመልከቻው ጠይቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ተፈናቃዮቹ ከተመለሱ በኋላ “የደህንነት ዋስትና እንዲያገኙ”፣ “መኖሪያ ቤታቸው እንዲመለስላቸው” እና “በዘላቂነት እንዲቋቋሙ” የሚያስችል ውሳኔ ከፍርድ ቤቱ ይጠብቃል። ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን በሚመለከትም፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት ተመሳሳይ ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስዱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት “ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብት ኢትዮጵያ” አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































