ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለማምለጥ በተደረገ ሙከራ፤ ቢያንስ አምስት ታራሚዎች ቆስለው መያዛቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ     

በአማኑኤል ይልቃል

በአዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የተወሰኑ ታራሚዎች ትላንት ለሊት ለማምለጥ ባደረጉት ሙከራ፤ አንድ እስረኛ ሲገደል ቢያንስ አምስቱ መቁሰላቸውን እና አንዱ ሳያይዝ መቅረቱን የአይን እማኞች እና የአካባቢ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ከቃሊቲ ማረሚያ ማዕከል የማምለጥ ሙከራ መደረጉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጠው የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ግን ያመለጠ እስረኛ “የለም” ብሏል።  

ከአስር ዓመት እና ከዚያ በላይ የተፈረደባቸው እስረኞችን ከሚያስተናግደው ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት የማምለጥ ሙከራ የተደረገው፤ ለዛሬ አጥቢያ ትላንት ረቡዕ ግንቦት 16፤ 2015 ለሊት አስር ሰዓት ገደማ መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የአይን እማኝ እና አምስት የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። የማምለጥ ሙከራውን ያደረጉት እስረኞች ብዛት 11 መሆኑን ከማረሚያ ቤት ፖሊሶች መስማታቸውን ነዋሪዎቹ አክለዋል። 

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ እስረኞቹ ከማረሚያ ቤቱ አምልጠው መውጣታቸውን ተከትሎ፤ በትንሹ ለአንድ ሰዓት ያህል የቆየ ተኩስ በአካባቢው ሲሰማ ቆይቷል። ድርጊቱ በተፈጸመበት ሰዓት በስራ ምክንያት በአካባቢው እንደነበሩ የተናገሩ አንድ የዓይን እማኝ በበኩላቸው፤ ተኩሱ ይበልጥ ጎልቶ ይሰማ የነበረው በማረሚያ ቤቱ መግቢያ ላይ ባለው አስፓልት መንገድ ላይ እና ተሻግሮ ባሉት አካባቢዎች እንደነበር አስረድተዋል። 

ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው ክራውን ሆቴል መግቢያ አካባቢ አንድ እስረኛ በጥይት ሲመታ ማየታቸውን የተናገሩት የዓይን እማኙ፤ የሆቴሉን መግቢያ አለፍ ብሎ በሚገኘው “ጋራዥ” አካባቢ ደግሞ ሌላ እስረኛ ተገድሎ መመልከታቸውን አስረድተዋል። “እኔ በትክክል ያየሁት አምስት ነው። አንደኛው ሞቷል። አራቱ ግን ገብተዋል” ሲሉ ለማምለጥ ከሞከሩት ውስጥ የተወሰኑት ተይዘው ወደ ማረሚያ ቤት ሲመለሱ ስለማየታቸው እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

አንዲት የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው የማምለጥ ሙከራ ካደረጉት እስረኞች መካከል በጥይት የቆሰሉት ስምንት መሆናቸውን ከማረሚያ ቤት ፖሊሶች መስማታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ብዙዎቹ እስረኞች “እግራቸው ላይ እንደተመቱ” ከፖሊሶቹ መረዳታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል። ሌላ የዓይን እማኝም፤ እግራቸውን የተመቱ እስረኞች በማረሚያ ቤቱ በሚገኘው ጤና ጣቢያ ህክምና ሲከታተሉ መመልከታቸውን አስረድተዋል። 

የዓይን እማኞቹም ሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ለማምለጥ ሙከራ ካደረጉት እስረኞች ውስጥ አንዱ እስካሁንም በፖሊሶች አለመያዙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢናገሩም የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገረመው አያሌው ግን ይህን አስተባብለዋል። ከእስር ቤት የማምለጥ ሙከራ መደረጉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት አቶ ገረመው፤ ያመለጠ እስረኛ ስለመኖሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ “የለም፤ ምንም የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

ጉዳዩ “ተጨማሪ ምርመራ ስለሚያስፈልገው” እና “በፖሊስ የተያዘ” መሆኑን የገለጹት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ አሁን ዝርዝር መረጃ መስጠት “ትክክል እንዳልሆነ” ተናግረዋል። እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ አንዲት የአካባቢው ነዋሪ ግን “ሊያመልጡ የነበሩ እስረኞችን ሊያጓጉዝ ነበር” ተብሎ የተጠረጠረ አንድ መኪና እና ሹፌሩ በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች መያዙን ተናግረዋል። የእስረኞቹን ጉዳይ ለማጣራት በስፍራው የተገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢም፤ በ“ሸገር ዳቦ” ማምረቻ ፋብሪካ አቅራቢያ አንድ የቤት መኪና በፌደራል ፖሊስ አባላት ምርምራ ሲደረግበት ታዝቧል። 

የፌደራል ፖሊስ አባላቱ በአስፓልት መንገድ ጥግ ላይ የቆመውን ይህን የቤት መኪና፤ ውስጡን እና ዙሪያውን ፎቶ ሲያስነሱ ለመመልከት ተችሏል። ከዚህ ምርመራ ሁለት ሰዓት ገደማ በኋላ፤ ይኸው መኪናው ከቦታው ሳይነሳ በሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት ሲጠበቅ ዘጋቢው ተመልክቷል። ከእነዚህ የፌደራል ፖሊስ አባላት በተጨማሪ የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ በርከት ያሉ የጸጥታ ኃይሎች በ“ፒክ አፕ” መኪና ላይ ሆነው በማረሚያ ቤቱ አካባቢ ሲዘዋወሩ ታይተዋል። 

የትላንት ለሊቱን የእስረኞች ማምለጥ ሙከራ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ወደ ማረሚያ ቤቱ ያመራው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ምላሽ የሚሰጠው አካል ሳያገኝ ቀርቷል። የማረሚያ ቤቱ ጥበቃዎች “አመራሮች አሁን ሌላ ጉዳይ ላይ ስለሆኑ መረጃ የሚሰጥ ሰው የለም” የሚል ምላሽ ለዘጋቢው ሰጥተውታል። ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ አቶ ጄይላን አብዲ፤ ይህ አይነቱ ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ነው ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት በበኩላቸው አሁን እየተደረገ ያለው ምርመራ ሲጠናቀቅ መስሪያ ቤታቸው መረጃውን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)