አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ75 ሀገራት ዜጎች የፍልሰት ቪዛ (immigrant visa) መስጠት እንደምታቆም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። የእነዚህ ሀገራት ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደ አሜሪካ እንዲገቡ የሚፈቅደውን የቪዛ አሰጣጥ የሚያቆመው ውሳኔ ከሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ጥር 13፤ 2018 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።
ውሳኔው የሚመለከተው፤ በአሜሪካ የሚገኙ ዜጎቻቸው “ተቀባይነት በሌለው መጠን” ከመንግሥት ድጎማ የሚቀበሉ ሀገራትን እንደሆነ ማርኮ ሩቢዮ የሚመሩት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ገልጿል። መሥሪያ ቤቱ በኤክስ ገጹ በኩል ባሰራጨው አጭር ማብራሪያ፤ ሶማሊያ እና ኤርትራ እገዳው ከሚመለከታቸው ሀገራት መካከል እንደተካተቱ በምሳሌነት ጠቅሷል።
የቪዛ ክልከላው “አዲስ ስደተኞች ከአሜሪካ ሕዝብ ሃብት እንደማይበዘብዙ” ሀገሪቱ እስክታረጋግጥ ድረስ የሚቆይ ነው ተብሏል። የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ፤ በአሜሪካ ቤተሰብ ወይም እጮኛ ላላቸው እና የሥራ ዕድል ላገኙ የሌሎች ለገራት ዜጎች ይሰጡ የነበሩ የቪዛ አይነቶችን ያካትታል።
ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች መካከል ከኬንያ እና ጅቡቲ በስተቀር የኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ዜጎች ወደ አሜሪካ በሚያስገባቸው የፍልሰተኛ ቪዛ ላይ እገዳ ተጥሎባቸዋል። የአሜሪካ የቅርብ አጋር የምትባለው ግብጽ፣ ሁለቱ ኮንጎዎች፣ ናይጄሪያ እና ሩዋንዳ ክልከላው ተግባራዋ ከሚደረግባቸው 75ቱ ሀገራት መካከል ተካትተዋል።
በሁለተኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመናቸው ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ አንድ ዓመት ሊሞላቸው የተቃረቡት ትራምፕ እና ቀኝ ዘመም ባለሥልጣኖቻቸው፤ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚደረገውን ፍልሰት ለመግታት መሰል እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል። የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በዲቪ ሎተሪ ለሌሎች ሀገራት ቪዛ የሚሰጥበትን አሰራር ከሶስት ሳምንታት በፊት ማቆሙ ለዚህ ተጠቃሽ ነው።
የእዚሁ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ክሪስቲ ኖም በኢትዮጵያ ግጭት ምክንያት ወደ አሜሪካ የገቡ ሰዎች በግዳጅ ወደ ሀገራቸው ከመመለስ የሚጠብቃቸውን ከለላ ከወር በፊት ማንሳታቸው የሚታወስ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































