ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ፍርደኞችን ለመለዋወጥ ያደረገችው ስምምነት በፓርላማ ሊጸድቅ ነው

የኢትዮጵያ መንግሥት ከቻይና እና ከብራዚል መንግሥታት ጋር “ፍርደኞችን ለማስተላለፍ” የተፈራረመው ስምምነት፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊጸድቅ ነው። ምክር ቤቱ ነገ ሐሙስ ጥር 7፤ 2018 በሚያካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተደረገውን “በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት” ስምምነትም መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ለነገው የፓርላማ ስብሰባ ከተያዙ ሰባት አጀንዳዎች መካከል አምስቱ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር የተፈራረመቻቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶችን የተመለከቱ ናቸው። የቻይና እና የኢትዮጵያ መንግሥታት ያደረጓቸው ሁለት ስምምነቶች በነገው አጀንዳ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ ይገኙበታል። 

የመጀመሪያው ስምምነት በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል በወንጀል ጉዳዮች ላይ “የጋራ የሕግ ትብብር” ለማድረግ የተደረገ ስምምነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሁለቱ ሀገራት መካከል “ፍርደኞችን ለማስተላለፍ” ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ነው። እነዚህ ስምምነቶች ባለፈው ህዳር 20 በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ በአዋጅ መልክ እንዲጸድቁ “በሙሉ ድምጽ” ለፓርላማ የተመሩ ናቸው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጆቹን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተላለፈው፤ “ስምምነቶቹ ቢጸድቁ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ውጤታማ የወንጀል መከላከል የሁለትዮሽ የህግ ትብብር የሕግ ማዕቀፍ ለመፍጠር የሚያስችላት መሆኑን በመገንዘብ” እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በወቅቱ አስታውቆ ነበር። በዚሁ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ፤ ኢትዮጵያ ከብራዚል እና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያደረገቻቸው ተመሳሳይ ስምምነቶችም ለፓርላማ እንዲቀርቡ ውሳኔ ተላልፎ ነበር። 

ኢትዮጵያ እና ከብራዚል ጋር ያደረገችው ስምምነት፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል “ፍርደኞችን ማስተላለፍን” የሚፈቅድ ነው። “በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠትን” የሚመለከተው ሌላው ስምምነት ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተደረገ ነው። በነገው የፓርላማ ስብሰባ፤ እነዚህን ስምምነቶች በተመለከተ የተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ ካቀረበ በኋላ በአዋጅ መልክ ይጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)